ወርሃዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁነቶች – ግንቦት 2009 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት (ኢሰመፕ) የተዘጋጀ
1. በአክቲቪስት ንግስት ይርጋ የሽብር ክስ መዝገብ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ባለመቅረባቸው ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠው ግንቦት 15/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት ነበር፡፡ በዚህ መዝገብ የሽብር ክስ የተከፈተባቸውን የስድስት ሰዎች ጉዳይ የሚመለከተው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ችሎት የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ግንቦት 15/2009 ቀጠሮ ይዞ የነበር ቢሆንም ምስክሮች ባለመቅረባቸው ተለዋጭ ቀጠሮ ሊሰጥ ችሏል፡፡ አቃቤ ህግ ምስክሮቹ ባስመዘገቡት አድራሻ ፖሊስ ሊያገኛቸው እንዳልቻለ ተጠቅሶ ረጅም ቀጠሮ እንዲሰጥ የሚጠይቅ ከፌደራል ፖሊስ ደብዳቤ ይዞ ቀርቧል።
ተከሳሾች በበኩላቸው ፖሊስ ባለፈው ቀጠሮ ምስክሮቹን ማቅረብ እንዳልቻለ ተናግሮ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁንም ማቅረብ አልቻልኩም እያለ ስለሆነ ተለዋጭ ቀጠሮ ሳይሰጥ የቀረቡ ማስረጃዎች ተመርምረው ብይን እንዲሰራ ጠይቀዋል። ተከሰሾች በእስር እንደሚገኙ በመግለጽ፣ ‹‹እኛን አስሮ ምስክር በማፈላለግ ሰበብ እየተጉላላን ነው›› ሲሉ አቤቱታ አሰምተዋል፡፡
በመዝገቡ 1ኛ የሆነችው አክቲቪስት ንግስት ይርጋ በእህቷ እንዳትጠየቅ ክልከላ እንደተደረገባትና ይህም በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 21(2) በጥበቃ ስር ስላሉ ሰዎች መብት ላይ የተደነገገውን የሚጥስ ነው ስትል አቤቱታ አሰምታለች፡፡ፍ/ቤቱ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ተፈላልገው ሲቀርቡ ምስክርነታቸውን ለማድመጥ በሚል ለሰኔ 20/2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
2. አክቲቪስት ዮናታን ተስፋዬ በተከሰሰበት የሽብርተኝነት ክስ ሙሉ በሙሉ ጥፋተኛ ተብሎ የ6 አመት ከ6 ወር እስር ቅጣት ተበይኖበታል
የሰሚያዊ ፓርቲ የቀድሞው ሕዝብ ግኙኝነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በተከሰሰበት የሽብርተኝነት ክስ ሙሉ በሙሉ ጥፋተኛ መሆኑን የፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ግንቦት 8 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት በይኗል፡፡ አክቲቪስት ዮናታን ተስፋዬ በተከሰሰበት የሽብር ክስ ጥፋተኛ የተባለው በስሙ በሚጠቀምበት የግል የፌስ ቡክ አካውንቱ የጻፋቸው ጽሁፎች በማስረጃነት ተቆጥረውበት ነው፡፡ ዮናታን ጥፋተኛ የተባለው የሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 አንቀጽ 6 ላይ የተመለከተውን ድንጋጌን በመተላለፍ መሆኑን ፍ/ቤቱ በጥፋተኛነት ፍርዱ ላይ አመልክቷል፡፡
በዚህም ፍርድ ቤቱ ግንቦት 17 ቀን 2009 ዓ.ም የቅጣት ውሳኔ ለማሳለፍ ተሰይሞ ተከሳሹ ለእስር ከተዳረገበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ በስድስት አመት ከስድስት ወር የእስር ቅጣት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡
3. ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ላይ በተመሳሳይ የጥፋተኛነት ፍርድ የተሰጠው ባሳለፍነው ግንቦት ወር ነበር
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ግንቦት 16/2009 ዓ. ም በዋለው ችሎት የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አንቀጽ 257(ሀ እና መ) የተመለከተውን ‹ግዙፍ ያልሆነ የወንጀል መሰናዳትና መገፋፋት ድርጊት› በመተላለፍ የአመጽ ማነሳሳት ወንጀል ፈጽሟል የጥፋተኝነት ፍርድ በሙሉ ድምጽ ማስተላለፉን ችሎቱ አስታውቋል፡፡ በዚህም ፍ/ቤቱ የቀረበለትን ግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየቶች እንደመረመረ በመግለጽ ግንቦት 18/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት የአንድ አመት ከስድስት ወር የእስር ቅጣት መወሰኑን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው እስካሁን በእስር ያሳለፈው ጊዜ ተሰልቶ በቂ ሆኖ ከተገኘ ከእስር እንዲፈታ ችሎቱ አሳስቧል፡፡
4. ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ እና ዳንኤል ሺበሺ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ ክስ ተመሰረቶባቸዋል
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ታስረው በፖሊስ ጣቢያ እስር ቤቶች ከ6 ወር በላይ በእስር የቆዩት ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩና አቶ ዳንኤል ሺበሽ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መተላለፍ የቀረበው ክስ ፍርድ ቤት ቀርበው ተነቦላቸዋል፡፡ ሁለቱ ተከሳሾች በዋናነት በአዋጁ የተከለከሉ መልዕክቶችን በግል የሞባይል ስልካቸው ይዘው ተገኝተዋል በሚል ክስ መቅረቡን ለመረዳት ተችሏል፡፡
ተከሰሾች የዋስትና መብታቸውን ተከልክለው በእስር ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በፌደራል ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በዚህም መሰረት ሁለቱም ተከሰሾች ወደ ቂሊንጦ እስር ቤት እንዲዛወሩ ተደርገዋል፡፡
5. ዶ/ር መረራ ጉዲና ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ብይን ባለመሰራቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል::የተለያዩ ክሶች ቀርበውባቸው በእስር የሚገኙት የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በቀረበባቸው ክስ ላይ ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ብይን ባለመሰራቱ ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠው ግንቦት 25/2009 ዓ.ም ነበር፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዳኞች የቀረበውን የክስ መቃወሚያ እና የአቃቤ ህግ አስተያየት በመመርመር ላይ እያሉ፤ በተመሳሳይ መዝገብ በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዢን (ኢሳት) እና በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦኤምኤን) ላይ የቀረበው ክስ (2ኛው ክስ) አቀራረብ ላይ ችግር በመመልከታቸው ብይኑን ለመስራት እንዳልቻሉ ተናግረዋል። ሁለቱ ተቋማት ህጋዊ ሰውነት አላቸው ወይ የሚለው በክሱ ባልተጠቀሰበት ሁኔታ የወንጀለኛ ህግ አንቀፅ 34(1)ን ማካተቱ ተገቢ እንዳልሆነ ተጠቅሷል፡፡ ስለሆነም ይህ ክስ ተስተካክሎ ከቀረበ በኋላ ዶ/ር መረራ ጉዲና በክሱ ላይ ባቀረቡት መቃወሚያ ላይ ብይኑ እንደሚሰጥ ዳኞች ተናግረው ቀጣይ ቀጠሮው ሰኔ 13/2009 መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
6. እነ ጉርሜሳ አያኖ/በቀለ ገርባ በተደጋጋሚ ለብይን በሚል ቀጠሮ እየተሰጠባቸው ይገኛል::በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ የተካተቱት የኦፌኮ አመራሮች በአቃቤ ህግ ማስረጃዎች ላይ ብይን ለመስራት በሚል ተደጋጋሚ ቀጠሮ እየተሰጠባቸው ይገኛል፡፡ ግንቦት 7/2009 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዞ አቃቢ ህግ ባቀረበው የሰው፣ የሰነድ እና የድምፅ ከምስል ማስረጃዎችን መርምሮ ብይን ለማሰማት ነበር። ሆኖም ዳኞች መዝገቡን የመመርመር ስራ እንዳላለቀላቸው በመግለጽ ለ5ኛ ጊዜ ለግንቦት 30/2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል። ሆኖም ግንቦት 30/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎትም መዝገቡን መርምሮ ብይን መስጠት ሳይቻል ለ6ኛ ጊዜ ቀጠሮ ሊሰጥ ችሏል፡፡ በዚህም ተከሳሾች መጉላላት እየደረሰባቸው መሆኑን አቤቱታ አሰምተዋል፡፡ችሎቱ አሁንም የመጨረሻ ቀጠሮ በማለት ብይኑን መርምሮ በንባብ ለማሰማት መዝገቡን ለሰኔ 9/2009 ዓ.ም ቀጥሯል።
7. የኢትዮጵያ መንግስት ከሳምንት ጊዜ በላይ የኢንተርኔት አገልግሎትን አቋርጦ ቆይቷል
ኢትዮጵያ ከግንቦት 23/2009 እስከ ሰኔ 01/2009 ዓ.ም የኢንተርኔት አገልግሎትን አቋርጣ ነበር፡፡ በጊዜው ቀደም ብሎ የኢንተርኔት አገልግሎቱ እንደሚቋረጥ የገለጸ አካል ባይኖርም፣ አገልግሎቱ ከተቋረጠ በኋላ በመንግስት የተገለጸው ምክንያት ለተማሪዎች ብሄራዊ ፈተና በሚል እንደሆነ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባወጀበት ሰሞን ኢንተርኔትን አቋርጦ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ የአሁኑ የአገልግሎት መቋረጥ በ2009 ዓ.ም ብቻ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *