የመንግስቱ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የእስረኞች መብት ጥሰትን አጣርቼ መብት ተጥሷል ለማለት ግን “በቂ መረጃ” አላገኘሁም አለ፡፡

አገናኝ ካሱ ደርሶ በእነ ገብሬ ንጉሴ ወልደየስ መዝገብ የፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ 3(1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በሚል አቃቤ ህግ በ2/4/2008 ክስ ከመሰረተባቸው 14 ሰዎች ውስጥ 2ኛ ተከሳሽ ነው። አገናኝ ካሱ ክስ “በአርበኞች ግንቦት 7 በአባልነት ከተመለመለ በኋላ ከታህሳስ ወር 2006 ጀምሮ ኤርትራ በመሄድ እና ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ፤ ከስልጠናው በኋላም የአመራርነት ተልእኮ በመውሰድ በክሱ ከተካተቱት ሌሎች ተከሳሾች ጋር ከሰኔ 25–28/2007 በመከላከያ ሰራዊት፣ የትግራይ ክልል ምእራባዊ ዞን ልዩ ሃይል እና የአካባቢው ሚኒሻዎች ጋር ውጉያ እያደረጉ እያሉ” በቁጥጥር ስር የዋለ መሆኑን የቀረበበት ክስ ያስረዳል።

አገናኝ ካሱ፤ ክስ ከተመሰረተበት በኋላ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኝ ሲሆን ነሃሴ 28/2008 በቂሊንጦ ማ/ቤት ለተከሰተው ቃጠሎ እና የሰው ህይወት መጥፋት ተጠያቂ ናችሁ ተብለው የወንጀል ክስ ከተመሰረተባቸው 121 እስረኞች ውስጥ አንዱ ነው፤ የቅሊንጦን ቃጠሎ ተከትሎ ሸዋሮቢት ተወስዶ ምርመራ በሚደረግበት ወቅት እንዲሁም ወደ ቂሊንጦ ከተመለሰ በኋላ ከፍተኛ ድብደባ እና ማሰቃየት እንደተፈፀመበት እና በማንነቱ ስድብ እና እንግልት እንደሚደርስበት፤ ባጠቃላይ በህገመንግስቱ የተደነገጉ ሰብአዊ መብቶቹ እንደተጣሱ ክሱን እየተከታተለ ላለው ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ችሎት አመልክቶ ነበር።

ዳኞቹም የማረሚያ ቤት ሃላፊዎች ቀርበው ምላሽ እንዲሰጡ አድርገው ነበር። የቀረቡት ሃላፊዎች ተከሳሹ  ያቀረበው አቤቱታ ሃሰት መሆኑን ቀርበው አስረድተዋል፤ በፅሁፍም ምላሽ ሰጥተዋል። አቤቱታውን ያቀረበው አገናኝ ካሱ፤ ከማረሚያ ቤት ሃላፊዎች የተሰጠው ምላሽ ከእውነት የራቀ መሆኑን መናገሩን ተከትሎ ዳኞቹ ጉዳዩ በገለልተኛ ወገን መጣራት እንዳለበት በመናገር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን አጣርቶ ሪፓርት እንዲያቀርብ አዘዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን አጣርቻለሁ በማለት መጋቢት 13/2009 ቀን የተፃፈ ሪፓርት ለ4ኛ ችሎት አቅርቧል። በሪፓርቱ አቤቱታ አቅራቢው አገናኝ ካሱ በሸዋሮቢት የደረሰበትን ጥሰት የሚያስረዱለት 3ት ምስክሮችን አቅርቦ ማሰማቱን ጠቅሰው የድርጊቱን ፈፃሚዎች ስማቸውን እና የመጡበትን ተቋም ግን ለይተው ባለማወቃቸው የማስረጃ እጥረት ማጋጠሙን ያትታል። በተጨማሪም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሃላፊዎችን ማናገራቸውን የሚጠቅሰው ሪፓርቱ፤ ተከሳሹ ያቀረቡት አቤቱታ በማረሚያ ቤቱ እንዳልተፈፀመ፣ በማንም ታራሚ ላይ እንደማይፈፀም፣ ምርመራ ሊካሄድ የሚችለውም ህግን መሰረት ባደረገ መልኩ በመሆኑ ተከሳሹ ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን መግለፃቸው በሪፓርቱ የተካተተ ሲሆን ሸዋሮቢት ስለተፈፀመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጉዳይ በተመለከተ የነሱ ሃላፊነት እስረኞቹን ወደ ሸዋሮቢት ማድረስ እንጂ ከዛ በኋላ ስለተከሰተው ነገር እንደማይመለከታቸው የቂሊንጦ ሃላፊዎች መናገራቸውን ይገልፃል።

የኮሚሽኑ ሪፓርት በማጠቃለያው ምርመራ የሚያካሂዱ የፌደራልም ሆነ የክልል ፓሊሶች ማንነታቸውን በግልፅ የሚያሳይ መታወቂያ ማንጠልጠል እንዳለባቸው እንዲሁም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በስሩ የሚገኙ እስረኞችን ጉዳይ መከታተል ግዴታቸው መሆኑን ይመክራል። ፕሮጅክታችን የነአገናኝ ካሱን የፍርድ ሂደት እየተከታተለ ባይዘግብም መንግስታዊው የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አከናወንኩ ያለውን የመብት ጥሰት ማጣራት ለማሳየት ኮሚሽኑ ለፍ/ቤት ያቀረበው ሙሉ ሪፓርት ከዚህ ፅሁፍ ጋር አያያዞ አቅርቧል።

EHRC’s report to F.high court 4th bench on Agenagn’s compliant–

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *