የተቃውሞ ድምጾችን ለማፈን› የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጭር ዳሰሳ፡- አዲስ አበባ እንደማሳያ

stateofemergencymgn
የአዋጁ ዓይነት፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
የታወጀበት ጊዜ፡- መስከረም 28/2009 ዓ.ም
ተፈጻሚ የሚሆንበት ጊዜ፡- ከመስከረም 27/2009 ዓ.ም ጀምሮ በሚታሰብ ለስድስት ወራት የሚቆይ
የተፈጻሚነት ወሰን፡- በመላ ኢትዮጵያ
በተወካዮች ም/ቤት የጸደቀበት ዕለት፡- ጥቅምት 10/2009 ዓ.ም
የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 93 (1) ላይ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይደነግጋል፡፡ በዚህ አንቀጽ ላይ እንደተመለከተው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ የሚገባው (የሚችለው) ‹‹የውጭ ወራሪ ሲያጋጥም ወይም ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማነኛውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት›› ነው፡፡ መንግስት አሁን ላይ በስራ ላይ ያለውንና መስከረም 28/2009 ዓ.ም በኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ም/ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የጠቀሰው መነሻም ይህንኑ የህገ-መንግስት ድንጋጌ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በህገ መንግስቱ ላይ እንደተቀመጠው አሁን ላይ ‹የውጭ ወራሪም ሆነ የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ› ባይከሰትም፣ መንግስት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮምያና አማራ ክልሎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮንሶ የገጠመውን ህዝባዊ ተቃውሞ፣ በተለይም በኦሮሞ የኢሬቻ በዓል አከባበር ወቅት ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ቁጣ፣ ‹ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ› ነው በሚል ሰበብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጅ ችሏል፡፡ መንግስት በእነዚህ አካባቢዎች የገጠመውን ህዝባዊ ተቃውሞ በኃይል ለማዳፈን በወሰደው የኃይል እርምጃ በትንሹ በኦሮምያ ከአምስት መቶ በላይ፣ እንዲሁም በአማራ ከአንድ መቶ የሚበልጡ ንጹሃንን መግደሉ ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈጸም በሚል በጠ/ሚኒስትሩ የሚመራ አባላቶቹ ይፋ ያልሆኑ ኮማንድ ፖስት ያቋቋመ ሲሆን፣ ኮማንድ ፖስቱ በበኩሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (እርምጃ) አፈጻጸም መመሪያን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ የአፈጻጸም መመሪያው ሦስት ክፍሎችን የያዘ ሲሆን በክፍል አንድ በአዋጁ የተከለከሉ ተግባራትን፣ በክፍል ሁለት የተከለከሉ ተግባራት ተፈጽመው ሲገኙ ስለሚወሰዱ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎች እንዲሁም በክፍል ሦስት ስለ ‹ተሀድሶና› ፍ/ቤት ስለማቅረብ የተቀመጡ ዝርዝር ተግባራትን ይዟል፡፡
ከእነዚህ ዝርዝሮች መካከል ትኩረትን የሳበው በክፍል አንድ የተቀመጡት የተከለከሉ ተግባራት (ድርጊቶች) ናቸው ተብለው የተጠቀሱት ጉዳዮች ናቸው፡፡ በዚህ ክፍል የተቀመጡትን ክልከላዎች ለተመለከተ በሀገሪቱ ‹‹ምንም ያልተከለከለ ነገር የለም›› በሚያስብል ደረጃ ጥብቅ ቁጥጥር የማድረግን ፍላጎት ያሳያል፡፡በዚህ አንቀጽ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብና ሌሎችም መሰረታዊ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ተሽረዋል፡፡
ከድርጊቶቹም መሃል . ‹ሁከትና ብጥብጥ› የሚያስነሳ ጽሁፍ ማዘጋጀት ( ቀድሞም በወንጀል ህግ የሚያስቀጣ) . ትዕይንት ማሳየት . መልዕክት በኢንተርኔት፣ በሞባይል በጽሁፍ፣ በቴሌቪዥን፣ በሬድዮ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ወይም በሌሎች የግንኙነት ዘዴዎች መለዋወጥ ( ምን አይነት መልእክት የሚለው ለትርጓሜ ክፍት የሆነ) . በሽብር ከተሰየሙ ቡድኖች/ድርጅቶች ጋር ማናቸውንም ግንኙነት ማድረግ . የቴሌቪዥን ወይም የሬዲዮ ፕሮግራሞችን መከታተል፣ የኢሳት፣ የኦኤምና የመሳሰሉት ሚዲያዎችን ማሳየት፣ መከታተልና ሪፖርት ማድረግ . ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ ማድረግ . ሱቅ አለመክፈት . ከስራ መቅረት . ያልተፈቀደ አልባሳት መልበስ . ያልተፈቀደ ቦታ መገኘት . ዲፕሎማቶች ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ርቀው እንዳይጓዙ (ከአንድ ወር በኋላ ክልከላው ተነስቷል) ….. እና ሌሎች በርካታ ክልከላዎች ተደንግገዋል፡፡
አዋጁን ተከትሎ በመንግስት እየተወሰደ ያለው እርምጃ፡- ጥቂት ጉዳዩች በአዲስ አበባ እንደማሳያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ወዲህ በሁለት ወራት ጊዜ ብቻ በመላ ሀገሪቱ በዘመቻ መልክ በሁለት ዙር 24,749 (ሀያ አራት ሺህ ሰባት መቶ አርባ ዘጠኝ) ኢትዮጵያውያን ለእስር ተዳርገዋል፤ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከላት (ማጎሪያ ስፍራዎች) ተግዘዋል፡፡ የተቃውሞ ድምጾች ታፍነዋል፤ ፕሬስ ውጤቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከህትመት ታግደዋል (ታዋቂውን አዲስ ስታንደርድ መጽሄትን መጥቀስ ይቻላል)፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በሀገሪቱ የሞባይል ኢንተርኔት ዳታ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ ቆይቷል፤ ማህበራዊ ሚዲያዎችና የተለያዩ አፕልኬሽኖች ተከርችመዋል፤ የግለሰቦች የሳተላይት ዲሾች ቤት ለቤት በሚያስሱ የመንግስት ኃይሎች እንዲወድሙ ተደርገዋል፡፡
መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመታወጁን አስፈላጊነት ሲገልጽ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎችና በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ አለመረጋጋቶችን ወደነበሩበት ሁኔታ ለመመለስ ነው ቢልም፣ በተግባር ግን ተቃውሞ ሰልፎች ባልነበሩባቸው አካባቢዎችም ጭምር፣ በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አማካኝነት የሰላማዊና ህጋዊ ተቃውሞ አራማጆችን ድምጽ ለማፈን አዋጁን እንደመሳሪያ ሲጠቀምበት ተስተውሏል፡፡
ለዚህ ጥሩ ማሳያ ደግሞ የሀገሪቱ ዋና መዲና አዲስ አበባ ናት፡፡ አዲስ አበባ በኦሮምያና አማራ ክልሎች እንደታየው አይነት ጉልህ ህዝባዊ ተቃውሞ አልተስተዋለባትም፡፡ ሆኖም ግን አዋጁ ከታወጀ ጊዜ ጀምሮ ሰላማዊና ህጋዊ የተቃውሞ ድምጽ በማሰማት የሚታወቁ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትን፣ ጋዜጠኞችን፣ ጦማርያንና አክቲቪስቶችን እያደኑ ማሰሩ ቀጥሏል፡፡ እስካሁንም በርካቶች ታስረዋል፡፡ ያሉበት የማይታወቁትም ብዙዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ወዲህ አዲስ አበባ ውስጥ ከታሰሩት በርካቶች መካከል ለማሳያነት ጥቂቶችን እንደሚከተለው አቅርቧል፡፡
1. ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የኦፌኮ ፕሬዚዳንትና የመድረክ ውጭ ግንኙነት ኃላፊ (ጠበቆቻቸውን እንዳያነጋግሩ ተከልክለው በሽብር ተግባር ምርመራ ሰበብ ማዕከላዊ በእስር ላይ ይገኛሉ)
2. አቶ ይድነቃቸው ከበደ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ም/ቤት ሰብሳቢ
3. መምህር አበበ አካሉ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ
4. አቶ ዳግማዊ ተሰማ፣ የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ኃላፊ የነበረ
5. አቶ ሰለሞን ስዩም፣ ደራሲና ጋዜጠኛ (የአንድነት ፓርቲ ጋዜጦች ኤዲቶሪያል ቦርድ ሰብሳቢ የነበረ)
6. አቶ እያስጴድ ተስፋዬ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባል የነበረና በማህረሰብ ሚዲያ አራማጅነት የሚታወቅ
7. አቶ ጠና ይታየው፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባል
8. አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል የነበረ
9. አቶ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ጋዜጠኛና የዞን 9 ጦማር ጦማሪ (ቪኦኤ አማርኛው ዝግጅት ላይ አዋጁን ተችተሃል በሚል የታሰረ)
10. አቶ አናንያ ሶሪ፣ ጋዜጠኛና የቀድሞው አንድነት ፓርቲ አባል የነበረ
11. አቶ ኤልያስ ገብሩ፣ ጋዜጠኛ
12. ወ/ት ብሌን መስፍን፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የነበረች (በፍ/ቤት ዋስ ቢፈቀድላትም ኮማንድ ፖስቱ ድጋሜ ያሰራት)
13. አቶ እዮኤል ዳምጤ፣ ጋዜጠኛ (በግል ጸብ ምክንያት ታስሮ ዋስ ቢፈቀድለትም ኮማንድ ፖስቱ ይፈልግሃል በሚል እስካሁን አስሮት ይገኛል)
14. አቶ አወቀ ተዘራ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባል (በፍ/ቤት በዋስ ቢለቀቅም ‹ማን ለቀቀህ› ተብሎ ድጋሜ በኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ የታሰረ)
15. አቶ ስዩም ተሾመ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህርና ጦማሪ (ከአዋጁ በፊት ቢታሰርም አሁን ላይ ጉዳዩ ወደኮማንድ ፖስቱ ዞሯል ተብሎ በእስር ላይ የሚገኝ)
16. አቶ መርከቡ ኃይሌ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባል
17. ወ/ት ወይንሸት ሞላ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባል
18. አቶ ሲሳይ አልታሰብ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባል
19. አቶ ኤፍሬም ሰለሞን፣ የአንድነት ፓርቲ አባል
20. አቶ አበበ ውቤ፣ የመኢአድ አባል
21. አቶ አስራት እሸቴ፣ የመኢአድ አባል
22. አቶ እዮብ ከበደ፣ የመኢአድ አባል (በ2000 ብር ዋስ ከተፈታ በኋላ ድጋሜ በኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ የታሰረ)
23. አቶ ሰመረ ወንዶሰን፣ የመኢአድ አባል
24. አቶ ፋንታሁን ብርሃኑ፣ የሰላም ማህበር ሊቀመንበር
እዚህ ለማሳያነት የተጠቀሱት ሰዎች የእስር ሁኔታ የሚመሳሰለው ሁሉም ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መታሰራቸው ሲሆን፣ ከታሰሩ በኋላ የተስተዋለው አካሄድ ግን ሦስት አይነት ነው፡፡
1. ከታሰሩ በኋላ ፍ/ቤት መቅረብ የቻሉ (የትኛውም የፍ/ቤት ትዕዛዝ ግን ያልተከበረላቸው)
2. ከታሰሩበት ዕለት ጀምሮ ፍ/ቤት ያልቀረቡ፣ ነግር ግን የታሰሩበት ምክንያት በታሰሩበት ቦታ የተነገራቸው
3. ስለታሰሩበት ምክንያት ምንም ያልተነገራቸው ወይም ያላወቁ ወይም እንዲያውቁ ያልተፈለጉ ናቸው፡፡
አዲስ አበባም ሆነ ከአዲስ አበባ ውጭ የታሰሩት ሰዎች በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ በተለያዩ የወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማት (ማጎሪያ ማዕከላት/concentration camp) ተግዘው፣ ጠያቂ ተከልክለው፣ ያሉበት ሁኔታ በውል ሳይታወቅ ወራትን እያስቆጠሩ ነው፡፡ ማስታወሻ -እስካሁን 24,799 ሰዎች እንደታሰሩ የገለጸው መንግስት ሲሆን ይሄ ቁጥር በምንም አይነት ገለልተኛ ተቋም አልተረጋጠም ፡፡


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *