የፖለቲካ ፓርቲዎቹ “ድርድር” መነሻና መድረሻ

22 የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀምጠው የጀመሩት “ድርድር” በተለያዩ አለመግባባቶች አሁን ቁጥራቸው በመመናመን 17 እንደደረሰ ሲዘገብ ሰንብቷል። ‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች “ድርድር” መነሻው እና አካሔዱ፣ እንዲሁም ተገማች መድረሻው ለመልካም አስተዳደር እና ዴሞክራሲያዊነት ይዞ የሚመጣው ተስፋ ይኖረው ይሆን?› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከዴሞክራሲ እና ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ዋና ዋና የፓለቲካ ሂደቶችን አስመልክቶ መረጃ ማጠናቀር አስፈላጊ ነው በሚል እሳቤ ከኢሰመፕ አእነንደየሚከተለውን ጽሁፍ አጠናቅረናል፡፡

ነገሩ ሁሉ ታሪካዊ ዳራ

በ1997 አገርዐቀፍ ምርጫ ገዢው ፓርቲ እና ተቃዋሚዎች በምርጫው ውጤት መስማማት አልቻሉም ነበር። ይህንን ተከትሎ ከፍተኛ ሕዝባዊ አመፅ ተቀሰቀሰ። አመፁን መንግሥት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን፣ የሲቪል ማኅበራትን እና የነጻ ሚዲያ አመራሮችን በማሰር አዳፈነው። በዚህ ብቻ አልተወሰነም። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር በተለያዩ አዋጆች እንዲጠብ ተደረገ። የመንግሥት የፀጥታ አካላት አዋጆቹ ከሚሰጡት በላይ ለጥጠው ተጠቅመውባቸዋል የሚልም ወቀሳ ይሰነዘራል። የዚህ ውጤት የተዳከመ ነጻ መገናኛ ብዙኃን፣ የተዳከሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የተዳከመ ፖለቲካዊ ተሳትፎ አስከተለ። ምርጫ 2002 በኢሕአዴግና አጋር/ደጋፊዎቹ 99.6 በመቶ አሸናፊነት ተጠናቀቀ። በ2007 የክልል እና የፌደራል ምክር ቤት ወንበሮች ሙሉ በሙሉ በኢሕአዴግ እና አጋሮቹ ተያዙ።

ይህ ወካይ እና መተንፈሻ ምኅዳር ማጣት የፈጠረው የሚመስለው ሕዝባዊ አመፅ በ2008 በብዙዎቹ የአገሪቷ አካባቢዎች ተቀጣጠለ። አመፁ ኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎችን አዳርሷል። መንግሥት በወሰደው አመፆቹን በኃይል የማስቆም ሙከራ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሞቱ። አገሪቷ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ቢያንስ ለ10 ወራት ወራት ያክል እና እና ገና እየቆጠረ ያለ ጊዜ እንድትቆይ ተገደደች። በብዙ ዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር ተዳረጉ። በዚህ መሐል ገዢው ፓርቲ የአመፆቹን መንስዔ “የመልካም አስተዳደር እጦት ሲሆን የተለያዩ አጀንዳዎች ያሏቸው ኃይሎች ጠምዝዘውታል” በሚል እየገለጸ ነው። ለዚህም ይመስላል “የተሐድሶ” ዘመቻ ጀምሬያለሁ ያለው። ከዚህ ጎን ለጎን የሚጠቀሰው ከፖለቲካዊ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ያደረገው ጥሪም የሕዝባዊ አመፁ ውጤት እንደሆነ ብዙዎች ጠርጥረዋል። “ድርድሩ” እንዴት እንደጀመረ ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡

የ“ድርድሩ” ታሪካዊ ዳራ

በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ፓርቲዎች መካከል እየተደረገ ያለው “ድርድር” የተጀመረው በኢሕአዴግ ጥሪ እንደሆነ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተደምጧል፡፡ ይሁን እንጂ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በዚህ አይስማሙም፡፡ እንደ አቶ የሺዋስ፣ በአገር ውስጥ እና በውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁሮች የተውጣጣ ቡድን ሰማያዊ ፓርቲ፣ መድረክ፣ ኢዴፓ እና መኢአድን ከኢሕአዴግ ጋር ለማነጋገር ጠይቆ፣ እና ሁሉም ፓርቲዎች ተስማምተው ከሕዳር 11 እስከ 13፣ 2009 ድረስ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ “ውይይት/ድርድር” ሊደረግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ምክንያት ተጨናግፏል፡፡

ይሁን እንጂ ይህንን አጀንዳ ከምሁራኑ በመቀማት፣ ኢሕአዴግ ራሱ የ“ድርድሩ” ጠሪ፣ መሪ፣ ቦታ ወሳኝ፣ አጀንዳ መራጭ ሆኖ እንደመጣ አቶ የሺዋስ ይናገራሉ፡፡ “በዚህ መንገድ ድርድሩን ገና ከጅምሩ በቁጥጥር ሥር አዋለው፡፡” የሆነው ሆኖ፣ ኢሕአዴግ “ለድርድር” ባደረገው ጥሪ 22 ፓርቲዎች ተገኝተው ውይይቱ ቀጥሏል፡፡

ኢሕአዴግ “ድርድሩን” ለምን ፈለገው?

ኢሕአዴግ “ድርድሩን” የጠራው ሕዝባዊ አመፅ አስጭንቆት ስለነበር እንደሆነ እና ሕዝባዊ አመፆቹን ለማስታገስ በመፈለግ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አቶ የሺዋስ ገና የድርድሩ መጀመሪያ ላይ ላቀረብንላቸው ተመሳሳይ ጥያቄ “ድርድሩን የሕዝቦች ቁጣ ለተቃዋሚዎቹ የሰጣቸው ዕድል” መሆኑን አልሸሸጉም፡፡ ይሁን እንጂ የድርድሩ ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ቀድሞ የታሰበበት እንደሚመስላቸውም አክለው ነግረውናል፡፡ እንደ አቶ የሺዋስ “ኢሕአዴግ ድርድሩን የፈለገው ቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2009 መደበኛ ጉባኤውን ሲጀምር ቃል የገባውን የምርጫ ስርዓት ለማሻሻል፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለይስሙላ በማሳተፍ በራሱ ፍላጎት መሠረት እንዲቋጭ ለማድረግ ነው፡፡”

በርግጥም፣ ኢሕአዴግ የክልል እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮችን ሙሉ ለሙሉ ማሸነፉን ባወጀ 7 ወር ጊዜያት ውስጥ ተቀስቅሶ ከዓመት በላይ ለዘለቀው ሕዝባዊ አመፅ በምላሹ ለመስጠት ቃል ከገባቸው ነገሮች ውስጥ ዐብይ የሚባለው የምርጫ ስርዓቱን አሁን ካለበት “First Past the Post (FPTP)” ወይም በየምርጫ ክልሉ የበለጠ ድምፅ ያገኘው ተመራጭ ብቻ ከሚያልፍበት ስርዓት ወደ “Proportional Representation (PR)” ወይም በሁሉም ምርጫ ክልሎች ፓርቲዎች ያገኟቸው ድምፆች ተደምረው እንደየምጣኔያቸው የምክር ቤት መቀመጫ የሚያገኙበት ስርዓት እንደሚቀየር ቃል ሲገቡ ነበር፡፡ ዶ/ር ሙላቱ በዓመቱ የምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ወቅት ቃል የገቡት “ባለፉት ምርጫዎች የገዠው ፓርቲ የበላይነት ታይቷል፡፡… ይህ የማይወከሉ ድምፆች እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ በምክር ቤቶቹ ውስጥ ሁሉንም የኅብረተሰብ ድምፅ ሊያሰማ የሚችል የምርጫ ሕግ ማሻሻያ ይደረጋል” በማለት ነው፡፡

 በሥያሜው ላይ የነበረው አለመግባባት

“ድርድሩ” ገና ከጅምሩ የገጠመው አለመግባባት ምን ተብሎ ይጠራ በሚለው ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ “የድርድሩ” ሥያሜ በኢሕአዴግ ባለሥልጣናት አጠራር በአማርኛ “ድርድር” ሲሆን፣ በእንግሊዝኛ ግን “dialog” (“ውይይት”) ተብሎ ነው የተጀመረው፡፡ በመቀጠል ግን “ድርድር”፣ “ውይይት” ወይም “ክርክር” ከሚለው አንዱ ወይም ሁሉም ይሁን በሚል ጊዜ ተሰጥቶት ተነጋግረውበታል፤ “ድርድሩ” በዚህ ምክንያት ቢያንስ ለአንድ ቀን ተስተጓጉሏል፡፡ በአቶ የሺዋስ አገላለጽ  በቅድመ ድርድሩ ወቅት  ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ “ድርድር” የሚለው ቀርቶ “ውይይት” ወይም “ክርክር” ይባል የሚለው ሲሆን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “እኛ የተደራጀነው ምርጫ ተወዳድረን ኢሕአዴግን በሥልጣን ለመተካት እንጂ እየተመካከርን ለመሥራት አይደለም” በሚል “ምክክር” ወይም “ውይይት” ይባል የተባለውን ውድቅ ሲያድርጉት፣ “ክርክርም ቢሆን ለምርጫ በማኒፌስቷችን መሠረት የምናደርገው እንጂ በዚህ ዓይነት ሁኔታ የሚደረግ ነገር አይደለም” በማለት ተቃውመውታል፡፡ በመረጨረሻም “ድርድር” ተብሎ እንዲጠራ ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን፣ በእንግሊዝኛ ምን ይባል የሚለው ላይ ውይይት ባለማድረጋቸው “dialog” እና “negotiation” በሚል በተለዋዋጭነት “ድርድሩን” ሲገልጽ ይታያል፡፡

እንዴት እየተዳረደሩ ነው?

የተዳራዳሪ ፓርቲዎቹን ቁጥር ከ22 ወደ 17 እንዲቀንስ ያደረገው ውድድሩ እንዴት ይደረግ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ከተነሱት ጥያቄዎች ውስጥ አራቱ ዐብይ አከራካሪ ጉዳዮች፣ አደራዳሪ ማን ይሁን? ታዛቢ ማን ይሁን? የሚድያ ሥነ ስርዓት ምን ይምሰል? የስብሰባው ሥነ ስርዓትስ? የሚሉት ነበሩ፡፡ አቶ የሺዋስ ታዛቢ ማን ይሁን በሚለው እና የሚዲያ ሥነ ስርዓቱ ምን ይምሰል በሚለው ላይ በሁሉም ፓርቲዎች መካከል ጠቅላላ መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ የመገናኛ ብዙኃን ስብሰባዎችን ሁሉ ገብተው እንዲከታተሉ፣ ነገር ግን ፓርቲዎቹ ባልፈለጉ ግዜ ስብሰባው በዝግ እንዲካሔድ መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ “አሁን ግን” ይላሉ አቶ የሺዋስ “በተቃራኒው ሚደያዎች የሚገቡት ፓርቲዎቹ እንዲገቡ በፈለጉ ግዜ ብቻ ነው”፡፡ በድርድሩ አካሔድ ላይ የተሻለ ተፅዕኖ እና መግባባት ለመፍጠር ሲባል ሰማያዊ፣ ከሌሎች አምስት ፓርቲዎች (ኢብአፓ፣ መኢዴፓ፣ ኢዴፓ፣ ኢራፓ እና መኢአድ) ጋር ግዜያዊ ኅብረት ነገር በመፍጠር እየተነጋገረ እንደነበር አቶ የሺዋስ ይጠቅሳሉ፡፡ መድረክ በበኩሉ፣ ራሱን ችሎ እንደስብስብ ፓርቲ ከመወከሉም በተጨማሪ ኦፌኮ እና ሶዴፓ “ድርድሩ” ውስጥ ተወክለው ስለነበር፣ ዘጠኙ ፓርቲዎች ጥሩ የመደራደሪያ አቅም ገንብተው “ድርድሩ”ም ተስፋ ሰጪ መስሎ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ኢሕአዴግ “ገለልተኛ አካል የለም” በሚል ምክንያት አደራዳሪ አያስፈልገንም የሚል አቋም ያዘ፡፡ በተጨማሪም፣ ስብሰባዎቹ “ድርድሩ” ውስጥ ባሉት ፓርቲዎች በዙር እንዲደረግ ጥያቄ አቀረበ፡፡ እንደ አቶ የሺዋስ ገለጻ ተቃዋሚዎች ገለልተኛ ናቸው የሚሉዋቸውን “12 ኢትዮጵያውያን” አነጋግረው ፈቃደኝነታቸውን ቢያገኙም በኢሕዴግ አለመስማማት “አደራዳሪ” ሊመርጡ አልቻሉም፡፡ በዚህ መግባቢያ ነጥብ ላይ መድረስ ባልቻሉበት ሁኔታ ላይ እያሉ “መድረክ [ከሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ጋር የምደራደርበት አጀንዳ የለኝም በሚል] ከኢሕአዴግ የሁለትዮሽ ድርድር” ጥያቄ አቀረበ፡፡ በዚህ የመድረክ ጥያቄ ላይ ከሌሎች ተቃዋሚዎች የቀረበ ተቃውሞ ባይኖርም፣ ኢሕአዴግ ባለመስማማቱ መድረክ እንዲሁም ሶዴፓ እና ኢዴፓ “ከድርድሩ” ራሳቸውን አገለሉ፡፡

መድረክ “ከድርድሩ” ራሱን ካገለለ በኋላም “አደራዳሪ” ይኑር አይኑር በሚል ቅድመ “ድርድር” የቀጠለ ቢሆንም “አደራዳሪ አያስፈልግም፤ ስብሰባው በዙር ይመራ” በሚለው ላይ ኢሕአዴግ አቋም በመያዙ፣ በተጨማሪም “አደራዳሪ ያስፈልጋል” ሲሉ የነበሩት ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም በኢሕአዴግ ሐሳብ በመስማማታቸው ሰማያዊ እና መኢአድ ራሳቸውን “ከድርድሩ” አግልለዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተደራዳሪዎቹ ቁጥር ከ22 ወደ 17 ዝቅ ብሏል፡፡

“በሕዝብ ሥም” እየተደራደሩ ያሉት እነማን ናቸው?

አሁን በመካሔድ ላይ ያለው ከገዢው ፓርቲ ጋር የመደራደር ዕድል የተገኘው “ሕዝቦች በቁጣ ለፓርቲዎቹ የሰጧቸው እንጂ ፓርቲዎቹ ታግለው ያገኙት እንዳልሆነ” አቶ የሺዋስ ያምናሉ፡፡ ይሁን እንጂ ገና ለድርድሩ ከመስማማታቸው ጀምሮ የተለያዩ ተቃውሞዎች እየቀረቡባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ ከሰማያዊ ፓርቲ ባለመግባባት ተገንጥሎ የወጣው እና በቀድሞው የፓርቲው ሊቀመንበር የሚመራው እና ራሱን “ሸንጎ” በሚል የሚጠራው ቡድን፣ ከመነሻው “ሕዝቦች ያስገኙት ዕድል መነጠቅ የለበትም፣ በቅድሚያ የፖለቲከኛ እስረኞች ይፈቱ” የሚል አቋም አራምዷል፡፡ የመደራደር አቅሙ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እስርቤት በታጎሩበት ሁኔታ ድርድር የሚባል ነገር እንደማይኖር የገለጹም ነበሩ፡፡ አረና ትግራይ ፓርቲ “በተለይ ዶ/ር መረራ ታስረው ድርድር አይኖርም” እስከማለት ደርሷል፡፡ በሌላ በኩል አራት የኦሮሞ ፓርቲዎች (ማለትም ኦአነግ፣ ኦነአግ፣ ኦብኮ፣ እና ኦነብፓ) በሚያዝያ ወር 2009 በሰጡት የጋራ መግለጫ “ፓርቲዎቹ እያደረጉት ያለው ድርድር የኦሮሞን ሕዝብ ችግር ፈትቶ የሕዝብን መብት ያስከብራል የሚል እምነት ስለሌላቸው ውጤቱ ምንም ይሁን ምን እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል”፡፡ “ድርድሩ”ን ዕውቆቹ መድረክ፣ ሰማያዊ እና መኢአድን የመሳሰሉት ፓርቲዎች ለቀው ከወጡ በኋላ የተነገረው ሌላ ዜና ደግሞ በሕዝብ ሥም እየተደራደሩ ያሉት እነማን ናቸው የሚለውን ጥያቄ አስፈላጊ አድርጎታል፡፡ ምርጫ ቦርድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ባስደመጠው ሪፖርት የሕግ መስፈርቶችን ያሟሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ብቻ ናቸው፤ ከነዚህ ውስጥ አገር ዐቀፎቹ አምስቱ ብቻ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በድርድሩ ላይ ያሉት አገር ዐቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች 17 ናቸው፤ ይህም ማለት ቀሪዎቹ 12ቱ ተደራዳሪዎች ሕጋዊ መስፈርቱን አሟልተው ዕውቅናቸውን ያደሱ ፓርቲዎች አይደሉም ማለት ነው፡፡ ይህ በቶሎ ተጣርቶ “በሕዝብ ሥም” አላግባብ የሚደራደሩ ፓርቲዎች እንዲለዩ ጥሪ ቀርቧል፡፡

“ድርድሩ ቆሟል”

“ድርድሩ” አሁንም ድረስ በቀሪዎቹ 17 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየተካሔደ ቢሆንም፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ግን ፓርቲያቸው “ድርድሩ ቆሟል” ብሎ እንደሚያምን ይናገራሉ፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ፣ “ኢሕአዴግ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ወደ ድርድር ሲገባ በአገሪቷ ተቀጣጥሎ የነበረው ሕዝባዊ አመፅ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በመቀዛቀዙ ምክንያት ‹የሚያስፈራው ነገር ስለሌለ› ኢሕአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር የነበረውን ፍላጎት አጥቷል፤ ስለዚህ ከጀመርኩት አይቀር ልግፋበት በሚል በይስሙላ እና በራሱ ፍላጎት ብቻ ነው እያስኬደው ያለው” ይላሉ፡፡ ለዚህም እንደምሳሌ የሚያሳዩት የኢሕአዴግ ተወካዮች ቀደም ሲል ያንፀባረቁትን ‹የማንደራደርበት አጀንዳ የለም› የሚል አቋም እየቀየሩ መሆኑን በቅርብ ጊዜ ከሰጡት ቃለ ምልልስ ጋር በማነፃፀር ይናገራሉ፡፡

Photo credit for Ethiopia News Network (ENN)

“ድርድሩ” ቀጥሏል

ሰማያዊ እና መድረክን የመሳሰሉት ፓርቲዎች ራሳቸውን ካገለሉም በኋላም ቢሆን “ድርድሩ” ቀጥሏል፡፡

ከዚያ ወዲህ 17 ፓርቲዎች ለብቻቸው የድርድሩ ታዛቢዎችን የሥነ ምግባር ደንብ አፅድቀዋል፣ሦስት አደራዳሪዎችን ከመሐከላቸው መርጠዋል፣ 13 የድርድር አጀንዳዎችን ጠቁመው ሰባቱን በማፅደቅ የቅድመ ድርድሩን ሒደት በይፋ ዘግተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙዎ “ወሳኝ” ናቸው ያሏቸው አጀንዳዎች ውድቅ ተደርገዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ “የፖለቲካ እስረኞች” መፈታት፣ የመሬት ፖሊሲው መሻሻል፣ የመገንጠል መብት ከሕገ መንግሥቱ መፋቅ፣ የትጥቅ ትግል የመረጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በድርድሩ እንዲሳተፉ ማድረግ የመሳሰሉት አጀንደዎች ተቀባይነት ያላገኙ አጀንዳዎች ናቸው፡፡

ከሰባቱ አጀንዳዎች መካከል ኢሕአዴግ የጠቆመው አንዱን ብቻ ሲሆን፣ ይኸውም “የምርጫ ሕጉን ማሻሻል” የሚለውን ብቻ ነው፡፡ ይህም አቶ የሺዋስ መጀመሪያ ላይ እንደጠቆሙት ኢሕአዴግ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ቃል የገባውን ‹የምርጫ ሕግ ማሻሻል› ጉዳይ በገዢው ፓርቲው የተወሰነውን በፓርቲዎች ድርድር የተገኘ ድል ለማስመሰል የመሞከር ሁኔታ እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡

የምርጫ ስርዓቱ አይሻሻልም

“ድርድሩ” በይፋ የተጀመረ ሰሞን ተቃዋሚዎች “ሕገ መንግሥቱን እስከመቀየር ድረስ” እንደሚደራደሩ የገለጹ ቢሆንም፣ ፓርቲዎቹ አጀንዳዎቻቸውን ማፅደቅ የጀመሩ ሰሞን ኢሕአዴግ “በሕገ መንግሥቱ ላይ የመደራደር መብት የለኝም” ብሏል፡፡ ነገር ግን “አብላጫ ድምፅ ያገኘ ተወዳዳሪ አሸናፊ የሚሆንበት የምርጫ ስርዓት” (FPTP) የተወሰነው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 መሠረት ነው፡፡ ኢሕአዴግ እንዲሻሻል የሚፈልገው ሌሎች የምርጫ ሒደቶችን የሚወስነውን የምርጫ ሕግ ከሆነ የምርጫ ስርዓቱ ላይም ቢሆን መሠረታዊ መሻሻል አይደረግም ማለት ነው የሚለው “ድርድሩ” ምንም መሠረታዊ ለውጥ ያመጣ ይሆናል የሚለውን ተስፋ የመጨረሻ ጭላንጭል ወስዶታል፡፡

ምን እንጠብቅ?

አቶ የሺዋስ በርሳቸው አነጋገር “ድርድሩ ባይቋረጥ ኖሮ” የተለያዩ አፋኝ አዋጆችን ፍቆ በመተካት፣ አዋጆቹን በሚያስፈፅሙ ከምርጫ ቦርድ እስከ እምባ ጠባቂ ባሉ ተቋማት ላይ የሚሾሙ አስፈፃሚዎች ምርጫ ላይ ተሳትፎ እስከማድረግ እንዲሁም በአንዳንድ የሕገ መንግሥት አንቀፆች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ይደራደሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ኢሕአዴግ “የሉም” ያላቸው የፖለቲከኛ እስረኞች ሳይፈቱ “ድርድር” የሚባል ነገር ውስጥ ላለመግባት ወስነው እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ እንደርሳቸው እምነት “እነዚህ መሠረታዊ ነገሮችን ከግምት ያላስገባ ድርድር ምንም በጉጉት የሚጠበቅ ውጤት አይኖረውም”፡፡

አቶ የሺዋስ “አሁን ካለንበት ችግር መውጣት የምንችለው በድርድር ብቻ ነው” ቢሉም፣ ኢሕአዴግ ተመልሶ ወደ ሐቀኛ ድርድር የሚገባው “ሌላ ሕዝባዊ ቁጣ ተነስቶ ካስደነገጠው ብቻ ነው” ይላሉ፡፡ አሁን ግን ድርድር አለ ከተባለ “እየተቀለደ ነው”፡፡

አቶ የሺዋስ በድርድሩ ዙሪያ ስናናግራቸው እንደመደምደሚያ የነገሩንን እኛም መዝጊያችን አድርገነዋል፣ “እዚህ አገር ጦርነትን የሚያመጣው ዴሞክራሲ አለመኖሩ አይደለም፤ ተስፋ አለመኖሩ ነው፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *