ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ለ3ኛ ጊዜ ፍርድ ለመስጠት በሚል ቀጠሮ ተሰጠበት (ሚያዝያ 20/2009 )

ነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው በተከሰሰበት የወንጀል ድርጊት ማስረጃዎችን ሰምቶ ያጠናቀቀው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በመዝገቡ ላይ የፍርድ ውሳኔ ለማሳለፍ በሚል ብቻ ለ3ኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ፍ/ቤቱ ለዛሬ ሚያዝያ 20/2009 ዓ.ም ፍርድ ለማሰማት በሚል ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም ‹‹ተከሳሹ የካቲት 30/2009 ዓ.ም በችሎት የሰጠው የተከሳሽነት መከላከያ ቃል ከድምጽ ወደ ጽሁፍ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር አልተያያዘልኝም›› በሚል ሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ለግንቦት 16/2009 ዓ.ም ይዟል፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ሚያዝያ 02/2009 ዓ.ም ለፍርድ ቀጠሮ በተሰጠው መሰረት ችሎት ፊት ቀርቦ ተለዋጭ ቀጠሮ ለዛሬ ሲሰጠው፣ ፍርዱ ላለመሰራቱ ተመሳሳይ ምክንያት ነበር ከችሎቱ የተሰጠው፡፡ በወቅቱ ተከሳሹ የተከሳሽነት ቃሉ ወደ ጽሁፍ ተገልብጦ እንዲቀርብለት ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጠው ጠይቆ ችሎቱ ‹‹ጥብቅ ትዕዛዝ›› ሰጥቶ የነበር ቢሆንም ትዕዛዙ ሳይፈጸም በመቅረቱ ፍርዱ ለዛሬ መድረስ አለመቻሉን ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዚህም ፍርድ ቤቱ የተከሳሽነት ቃሉ ወደ ጽሁፍ ተገልብጦ እንዲያያዝለት በድጋሚ ጥብቅ ትዕዛዝ በመስጠት መዝገቡ ላይ ግንቦት 16/2009 ዓ.ም ፍርድ ለማሰማት ቀጥሮዋል፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ለፍ/ቤት ከሰጠው የተከሳሽነት መከላከያ ቃል በተጨማሪ በምርመራ ወቅት ለፖሊስ የሰጠውን ቃልም በመከላከያ ማስረጃነት አያይዞ አቅርቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *