የነጻ ዳኝነት ፍዳ በኢትዮጵያ

በመንግሥት አካላት በመኖሪያው አካባቢ፣ በአደባባይ የተደበደበው ዳኛ ይናገራል

አሰናኝ፦ ጌታቸው ወርቁ

እንተዋወቅ!

ብርሃኑ ታዬ እባላለሁ፤ ከ1992 እስከ 1999 መጀመሪያ ድረስ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና በፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በተለያየ ጊዜ በዳኝነት አገልግያለሁ፡፡ ከዛም በሁኔታዎች አስገዳጅነት ሥራዬን በፈቃዴ ለቅቄያለሁ፡፡ ከዚያ በኋላም ጥብቅና ሞያ ቆይቻለሁ፡፡ በተጓዳኝ በግልና በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋምት በሕግ የትምህርት ክፍል በትርፍ ሰዓት ሳስተምር ቆይቻለሁ፡፡

ሕይወት እንዴት ነበር?

እኔ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የደሃ ቤተሰብ ከሚባለው ነው የወጣሁት፡፡ አባቴ የቀድሞው የኢትዮጵያ ወታደር ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመርቄ በረዳት ዳኝነት ስሾምም በአግባቡ ሥራዬንና ሙያዬን አክባሪ ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ አፈፃፀማቸው ጥሩ ነው ከተባሉ ዳኞች አንዱ ነበርኩ፡፡ በሥራዬ ጥራትም፣ ብዛትም በአስተዳደሩም፣ በባልደረቦቼም ተመስጋኝ ዳኛ ነበርኩ፡፡ በዚህ የተነሳም በፍጥነት ለሙሉ ዳኝነት ከተሾሙት አንዱ ነበርኩ፡፡ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር በነበረኝ ግንኙነት፣ በአስተዳደሩም በጥሩ የምታይ ሰው ነበርኩ፡፡ እስከ 1997 ሀገራዊ የምርጫ ጉዳይ እስኪመጣ ድረስ ሥራዬን በአግባቡ እያከናወንኩ፤ አግባብ ያለው አዎንታዊ ምላሽ እያገኘሁ የምኖር ደስተኛ ሰው ነበርኩ፡፡

ሆኖም ከ1997 ምርጫ ጋር ተያይዞ የምርጫ ጉዳዮችን በፍርድ ቤት ማየት ስንጀምር ግን፣ ነገሮች እንዳልነበሩ ሆኑ፡፡ ፊት በማጥቆር ጀምሮ፣ በኋላ ጉዳዩ እኔን በተከበርኩበት አካባቢዬ ከእነ ታናሽ ወንድሜ በመደብደብና በማሰር ተጠናቆ፣ የዳኝነት ሥራዬን በጫና እስክለቅ ድረስ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት፡፡ የድቅድቅ ጨለማ ወቅት፡፡ ሆኖም ዛሬ የብርሃን ጮራ በመታየቱ በረዱኝ ሰዎች ላይ የሚደርስ ችግር ባለመኖሩና ፍርድ ቤቶችን በማሻሻሉ ሂደት ላይ ሊጥቅም ይችላል በሚል የሆነውን በመጠኑ ልናገር ችያለሁ፡፡

ሕይወትዎ እንዴት አስቸጋሪ ሊሆን ቻለ?

የደረሰብኝን ሁሉ በዝርዝር ለመናገር ጊዜው ገና ነው፤ ነገሮች ሙሉ ለሙሉ የፀዱ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም፣ የተወሰኑትን መረጃዎች መስጠት ይቻላል፡፡ የሰዎችን ሥም አልገልጽም፡፡ ግን ዋና ዋናውን ነገር መንገር እችላለሁ፡፡

እንደሚታወቀው፣ የ1997 የምርጫ ውድድድር ፉክክር እየጋለ መጥቶ በስተመጨረሻ የሚያዚያ 30 ሠልፍ እስኪካሄድ ድረስ ደህና ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የሚያዚያ 30 ሠልፍ ከተካሄደ በኋላ ግን ፍርድ ቤቶች ላይ የነበረው ጫና በእጅጉ ጨምሯል ማለት ይቻላል፡፡ በብዙኃን መገናኛው የሚፃፈው ነገር ዳኞች ላይ ያሳርፍ የነበረው ጫና ቀላል አልነበረም፡፡ በቤተሰብ ላይ የሚፈጠር ጫና አለ፡፡ በግልም፣ በጎንም በቡድንም አንተ (ዳኛ) ላይ ጫና ለመፍጠር የሚደረጉ የተለያዩ ጫናዎች ነበሩ፡፡ አስተዳደራዊ ጫና አንዱና ዋናው ነበር፡፡ በተለይ በከፍተኛው ፍርድ ቤት የምርጫውን ጉዳይ የምንመለከት ሁለት ዳኞች ነበርን፡፡ የመጀመሪያውን ፍርድ እንደሰጠሁ የነበረው ጫና ትልቅና ዓይነተ ብዙ ነበር፡፡

በምርጫ ተፎካካሪዎች የሚሰጡ መግለጫዎችንና ጫናዎችን መቋቋም የሚጠይቅ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር። መንግሥታዊ ጫና ትልቅ ቢሆንም፣ ከተቃዋሚ ጎራ የሚመጣው ጫናም ቀላል አልነበረም፡፡ ለጉዳዩ ጉጉ እና ስጉ የሆነው ማህበረሰብም (ገለልተኛው ወገን) የእርሱም ሁኔታውን ይመለከትበት የነበረው ሁኔታ ለዳኞች ጫና ነበረው፡፡ ፍርድ ቤቱ ላይ አንዳንዱ ተስፋ በመቁረጥ፣ ሌላው ምንም ሊሰሩ አይችሉም በሚል የሚያሳዩት ግብረ መልስ ለዳኞች ከፍተኛ ጫና ነበረው፡፡ ይሄ እየተካሄደ ሳለ፣ ትንሽ ጎላ ብሎ የሚታየው፣ የሲቭል (ሲቪክ) ማኅበራት የሚባሉት ምርጫ እንዳይታዘቡ በምርጫ ቦርድ ተከልክለው ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹እናንተ የተቋቋማችሁበት ዓላማ ምርጫን መታዘብ አያስችልም›› የሚል ነበር፡፡

በአጋጣሚ ይሄ ጉዳይ በሚታይበት ወቅት፣ እኔ እየሰራሁ በሕግ የድህረ ምረቃ ተማሪ ነበርኩ፡፡ በዛም የተነሳ አብረውኝ የሚሰሩ አንድ ሌላ ዳኛ ነበሩ፡፡ ሁለት ዳኛ ሆነን ነበር ፕሮግራም አውጥተን አንድ ሳምንት እኔ አንድ ሳምንት እሳቸው ሆነን ነበር ይህን ጉዳይ የምንሰራው፡፡

በዚህ ሁኔታ በምንሰራ ሰዓት፣ እሳቸው ጀምረውት ማስረጃ ሰምተው ቀጠሮ የሰጡት ፋይል እኔ ጋር መጣ፡፡ ይሄ ብዙ የሲቭክ ማኅበራት የተሳተፉበት የሲቭክ ማኅበራት ቅንጅት የሚባለው አለ፤ እነሱ ነበሩ ክሱን መስርተው የነበሩት፡፡ መዝገቡ ወደ እኔ ሲመጣ የሚከራከሩበት፣ ማስረጃ የሚሰማበት ሁኔታ ያን ያህል የተወሳሰበ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ እስከ ማስታውሰው ጭብጦቹ ሁለት ነበሩ፡፡

  1. የሲቪክ ማኅበራቱ በመተዳደሪያ ደንባቸው ምርጫ የመታዘብ ዓላማ አላቸው ወይ!?
  2. ሲቪክ ማኅበራት ምርጫ እንዳይታዘቡ የሚከለክል ሕግ ወይም ደንብ አለ ወይ? የሚሉ ነበሩ።

ስለዚህ ሳጣራ፣ ምርጫ ቦርድ በራሱ ብቻ እንደከለከላቸው ግልጽ ሆነ፡፡ እንዲሁም ለሃይማኖት ተቋማት ምርጫ ታዘቡ የሚል የመተዳደሪያ ደንብ ሳይኖራቸው ‹‹ለሃይማኖታቸው ሲሉ እውነቱን ይመስክራሉ›› በሚል እንዲታዘብ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ እነዚህ ሃይማኖተኛ ስለሆኑ እውነት ይናገራሉ፤ እነዚህ ደግሞ ሃይማኖተኛ ስላይደሉ እውነት አይናገሩም የሚል ብቻ ነው ማለት ነው፡፡

ይሄን በአዳሪ አየሁና ውሳኔ ሰጠሁ፤ ውሳኔው፡- አንደኛ ምርጫ ቦርድ ሲቭክ ማኅበራቱ ምርጫውን እንዳይታዘቡ የሚከለክልበት ምንም ሕጋዊ ድጋፍ የለውም፤ ሁለተኛ በወቅቱ ይሄን ሕግ ሲቪክ ማህበራቱን የሚያስተዳድረው ሕግ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ብቻ ነበረ፡፡ በኋላ ነው አዳዲስ ሕጎች የወጡት፡፡ ያኔ በፍትሕአብሔር ሕጉ ላይ በምናይበት ሰዓት ማኅበራት በቅድሚያ መስራት ያለባቸው ዓላማቸውን ነው፡፡ ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ከዓላማቸው ጋር የማይጋጭ ሌሎች ተግባራትን ማከናወን ሕጉ ይፈቅዳል፡፡ ይሄን ጠቀስኩ፤ ሌላው ደግሞ እነዚህ ተቋማት ህብረተሰቡን የሚወክሉ ናቸው፡፡ ይህን ግራ ቀኙ ያመኑት በመሆኑ አላከራክርም፡፡ አንዳንዱ ማህበራት የሴቶች ጉዳይ የሚወክሉ፣ አንዳንዱ የህፃናት ጉዳይን የሚወክሉ፣ ሌሎቹ ድህነትን ለመቅረፍ የሚንቀሳቀሱ አንዳንዶቹ ደግሞ ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰሩ ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ እነዚህ ተቋማት የህብረተሰቡን ጥቅም ለማስከበር የሚሰሩ ናቸው፡፡ ‹‹ፕሬዠር ግሩፕ›› ቢሆኑም ማለት ነው፡፡

የምርጫ አንዱ ዓላማ ደግሞ የህብረተሰቡን ጥቅም ያስከብራል የሚባል ፓሪቲ የሚመረጥበት ሂደት ነው፡፡ የህብረተሰቡን ጥቅም ያስከብራል የሚባል ፓርቲ ለመወዳደር ምርጫ በሚያደርግበት ሰዓት እነርሱ በድህነትም ይሁን፣ በሴት መብትም ይሁን የሚከራከሩትን ምርጫውን እንዳይታዘቡ ማድረግ ምንም ዓይነት የሕግ፣ የሕገመንግስት ድጋፍ የለውም፡፡ ፍትሐብሔር ሕጉ ደግሞ ይፈቅዳል፤ የምርጫ ሕጎችም ገደብ የላቸውም፤ በሕገ መንግሥቱ እንደውም እነዚህ ሰዎች ብዙውን ማህበረሰብ ሊወክሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ የምርጫ ሕጉንም የፍትሐ ብሔር ሕጉንም አጣቀስኩና ‹‹እነዚህ የሲቭክ ማህበራት፣ ምርጫውን ሊታዘቡ ይገባል›› የሚል ውሳኔ ሰጠሁ፡፡ ውሳኔው በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ወጣ፡፡ ከዛ በኋላ ነገሮች ሁሉ ደስ የማይሉ እየሆኑ መጡ፡፡

ይሄ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ አፈፃፀሙ ወዲያው ተጀመረ፡፡ ይሄን ከሰራሁ በኋላ ደግሞ ሌሎች ሲቪክ ማሕበራት በሌላ መዝገብ ተመሳሳይ ፍርድ አገኙ። በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ እኔ ለትምህርት የማርፍበት ወቅት ነው፤ ሌላኛው ዳኛ አፈፃፀሙን ጨረሱ፡፡ እኔ የሰጠሁት ውሳኔ እስከ ሰበር ችሎት ድረስ ሄዶ ጸንቷል፡፡

አሁን ሌላም ዳኛ የሰሩትን ሥራ ሁሉ እኔ እንደሰራሁት ተደርጎ ነው ይመለከተናል ለሚሉ ሥልጣን ላይ ላሉ የመንግሥት ኃላፊዎች ሪፖርት የተደረገው፤ ማን እንዳደረገው ግን አላውቅም፡፡ ያሰቡት ምንድን ነው፣ ምርጫ ቦርድም ለኔ ይወሰንልኛል ብሎ አስቧል- ያኔ፡፡ የጠየቋቸው ጥያቄ ዓላማቸው ላይ አለ ወይ ስል፣ የለም ብለዋል፣ እነርሱንም ዓላማቸው ላይ ስለሌለ ነው የከለከላችኋቸው ብዬ ስጠይቃቸው በደስተኝነት ‹‹አዎን›› ብለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት እናሸንፋለን ብለው አስበዋል፡፡ እኔ ግን ይወሰንላችኋል አላልኩም፡፡ እነርሱ ግምታቸውን ወስደዋል፤ ሁለቱም እንደሚያሸንፉ ተስፋ አድርገው ነው የሄዱት፡፡ የሆነው ይህ ነው፡፡ በዛ ወቅት ደግሞ ዓለማቀፍ ታዛቢዎችም ጉዳዩን ይከታተሉት ነበር፡፡

 በሕይወትዎ ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ? 

እንግዲህ መንግሥት ይላካቸው፣ አይላካቸው እኔ ማወቅ አልችልም፡፡ በመንግሥት ውስጥ ሌላ ድብቅ መንግሥት ይኑር አይኑርም አላውቅም፤ በግል ጥላቻ ብቻ ያን ሁሉ መከራ እንዲደርስብኝ ማድረግ ይቻላል ለማለትም ይከብዳል። እስከዚህ ጊዜ ድረስ በዙሪያዬ ሲከናወን ስለለበረው ምንም ነገር አላውቅም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ነገሮችን በተጨባጭና በአንክሮ ማስተዋል የጀመርኩት ከዚያ በኋላ ነው፡፡ እኔን ወደ ገዢውም ሆነ ተቃዋሚው ወገን ለመሳብ የሚደረጉ ጥረቶችን ፊት አልሰጠሁም፡፡ ምክንያቱም ዳኞች በገለልተኝነት፥ ለሕግና ለሕሊናቸው በመታመን መሥራት አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ዳኝነቴን ብቻ ነበር በገለልተኝነት መሥራት የምፈልገው፡

በኋላ ያስተዋልኩት ግን ፍርድ ቤት ውስጥ ራሱ ትሥሥሮሽ (ኔት ዎርኪንግ) እንዳለ አመላካች ነገሮች አየሁ፡፡ በሥራ አጋጣሚ በተለያየ ምክንያት የምታገኛቸውም ሰዎች፣ ተራ ሠራተኞች ብቻ እንዳልሆኑ ማስተዋልና አጠራጣሪ ተግባራቸውን መመልከት ጀመርኩ፡፡ ይህን ተከትሎም እኔ ላይ መዛት፣ ማስፈራራት፣ ጫና መፍጠር ጀመሩ፡፡

ከምርጫው በኋላ ደግሞ ሌሎች ጣጣዎች መምጣት ጀመሩ፡፡ ለምሳሌ ሁለት ጉዳዮች መጡ፤ አንደኛው በጣም የሚታወቀው ‹‹የምርጫው ውጤት ይሰረዝ›› የሚል አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ክስ ይመሰርታል፡፡ እሱን ክስ አሁንም ሌላኛው ዳኛ ይጀምሩትና ውሳኔው እኔ ጋ ይመጣል፡፡ ውሳኔውን ካዘጋጀውና ከጨረስኩ በኋላ ዛቻና ማስፈራራት ደረሰብኝ፡፡ የውሳኔዬ ይዘት አልተነገረም (ዲክለር) አልተደረገም፡፡

ጊዜው ሰኔ መጀመሪያ 1997 ነበር። ረብሻ በየቦታው ተካሂዶ ምርጫ ውጤት መግለጽ አልተቻለም፤ ቆጠራም አልተከናወነም እየተባለ ነበር፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ ጣልቃ ይገባና ውጤት እንዲገለጽ ያደርጋል፡፡ እኔ በወቅቱ ያየሁት፣ የተረዳሁት፣ ምርጫ ቦርድ ጣልቃ መግባቱ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ልክ ነው፡፡ ይህን አድርግ የሚል አንቀጾች ባይኖሩትም፡፡ አጠቃላይ የዓዋጁ ዓላም ግን የምርጫ ጉዳዮችን ምርጫ ቦርድ እንዲያስተዳድር ተፈቅዷል፡፡ ቦርዱ ጣልቃ ሲገባ ውጤቱን የገለጸው ጊዜያዊ ውጤት በሚል በሀገር አቀፍ ደረጃ ነው፡፡ በምርጫ ሕጉ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የምርጫ ውጤት የሚገለጸው በየደረጃው (በምርጫ ጣቢያ፥ ወረዳ፥ ክልል) ከተገለጸና ተገቢው የማጣራት ሥራዎች በየደረጃዎች ከተሰሩና ለቅሬታዎች በየደረጃው መፍትሔ ከተሰጠ በኋላ ሊሆን ይገባል፡፡ የምርጫ ውጤቶቹ መገለጽ ባለባቸው ደረጃዎች በየእርከኑ መለጠፍም ካለባቸው እየለጠፍክ ነው ማሳወቅ የሚገባው፥ በኔ አረዳድ። ማለትም በወቅቱ በነበረው ሕግ መሠረት በምርጫ ጣቢያ፣ በምርጫ ክልል፣ ከጨረስክ በኋላ ነው ወደ አገር አቀፍ ይግባኝም ካለ ከጨረሰ በኋላ ነው ምርጫ ቦርድ አረጋግጦ ውጤቱን የሚገልጸው፡፡

ያኔ በተግባር ፍርድ ቤቱንም የመፈተሸ ነገር ያለ ይመስለኛል። እንጂ ምርጫ ቦርድ ክሱ በቀረበበት ሰዓት፣ በትክክል ካስታወስኩት ከተወካዮች ምክርቤት መቀመጫዎች ውስጥ፤ ምርጫ ቦርድ ሳያሳውቅ የቀረው ወንበር ሰባት ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ቴክኒካሊ›› ስትወስደው ያን ያህልም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለውጥ የሚያመጣም አልነበረም፡፡ ግን እንደዚህ ዓይነት አቅጣጫ እንሂድና ምርጫ ቦርድ የሄደበትን መንገድ ልክ እንዳልሆነ የሚያሳይ ውሳኔ እንደተሰራ መረጃ ይኑር አይኑር አላውቅም፤ ገና ማታ ቤት እንዳለሁ ችግር ተጀመረ፡፡

እኔ ላይ በስልክ ዛቻ ተጀመረ፡፡ በአካልም በስልክም፣ ራሳቸውን የመንግስቱ ዋና አካል አድርገው የሚቆጥሩ የማላውቃቸው ሰዎች ተዘባበቱብኝ፣ ዛቱብኝ፡፡ ‹‹አርፈህ ቁጭ በል፤ እንቢ የምትል ከሆነ ደግሞ በአንተና በቤተሰብህ ላይ ችግር ይደርሳል፤ እናሳይሃለን፡፡ ባለፈው ምረንሃል፤ አሁን ግን አንለቅህም›› የሚል ነበር- ዛቻው፡፡ ‹‹ባለፈው›› ያሉት ሲቪክ ማኅበራት ምርጫ ይታዘቡ፣ አይታዘቡ የሚለውን ‹‹ይታዘቡ›› ብዬ ውሳኔ ማለፌ ነው፡፡

ይበልጥ ጥርስ ያስነከሰብኝ ደግሞ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት የተፈቀደላቸው የሲቪክ ማኅበራት ምርጫውን ለመታዘብ በሄዱባቸው ቦታዎች፣ ቅንጅትና ህብረት የተባሉት ፓርቲዎች ምርጫውን በብዛት አሸንፈዋል መባሉ ነበር፡፡ ከተሞች ላይ በሙሉ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በአብዛኛው ተሸንፎ ነበር፡፡ (በኋላ እንደተረዳሁት፥ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሲሰጥና ሲያስፈጽም ለምርጫው የቀረው ጊዜ አጭር ነበር፤ እና እነዚህ ማኅበራት የምርጫ ታዛቢዎቻቸውን ሊያሰራጩ የቻሉት በከተሞች ላይ ብቻ ነበር)

እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ነው ጥርስ ውስጥ የገባሁት፡፡ በኹነቱ ውስጥ እኔ እንዳለሁበት አድርገውም ያሰቡ ይመስላሉ፡፡ ነገሮችን ይበልጥ ያወሳሰበው ወደ ገዢው ፓርቲ ለመጠጋት አለመፈለጌ፤ የተቃዋሚው ጎራ እንደሆንኩ አድርገው ማመናቸው አንዱ ነው፡፡ ለተቃዋሚው ወገን ምንም አይነት ዝንባሌ አለማሳየቴ፤ በፍጥነት ከተሾሙት ዳኞች አንዱ በመሆኔ ይሄን እንደ ማረጋገጫ ወስደው የኢህአዴግ ፓርቲ አባል ነው ብለው የሚከራከሩም እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ በግል ችግራቸው የተነሳ ሐሜት የሚያሰራጩትና በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ትኩሳትና ስሜት ሲጨመርበት ያለምንም ተከራካሪ ወገን ለአደጋ አጋልጦኟል፡፡

እንግዲህ ከምርጫው በፊት በታዛቢዎች ውሳኔ ጥርስ ውስጥ ገባሁ፡፡ ከምርጫው በኋላ ደግሞ፣ የጻፍኩትና ላነብ ያዘጋጅሁት ውሳኔ አለ፡፡ ልክ ዛቻ ሲመጣብኝ፥ ከፕሬዝዳንቶች ለአንዱ ዛቻ እንደደረሰብኝ ሪፖርት አድርጌያለሁ፡፡

ቢቻል ጥበቃ ለማግኘት፤ ካልሆነ ከዳኝነት ሥራዬ በደረሰብኝ ጫና ምክንያት ልነሳ ባስብም ‹‹የመንግሥትን ሥም ያጠፋል›› የሚል ምክንያት በመሰንዘሩ አልቻልኩም። ጉዳዩን የምንመለከተው ሦስት ዳኞች እንድንሆን ሐሳብም አንስቻለሁ፡፡ (ምክንያቱም፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የማቋቋሚያ ዓዋጁ ላይ በአንድ ዳኛ የሚታይና በሦስት ዳኛ መታየት ካለበት ሦስት ዳኛ እንዲሆን ማድረግ ይችላል ይላል፡፡) ‹‹አይ! ቀደም ሲል አንተ ብቻህን እያየኸው ስለነበረ፣ ከአሁን በፊት በወሰንከው ደግሞ ዝናን ስላገኘህ፣ ሦስት ብናደርግህ አላሰራ አሉት የሚል ትርጉም ይፈጥራል፤ በተለይ ውሳኔው እኛን የማይደግፍ ከሆነ›› የሚል ምክንያት ቀረበልኝ፡፡

የውሳኔው ይዘት ምንም ሆነ ምን ካስፈለገ ጉዳዩ ስለከበደኝ ሦስት ዳኛ ሆነን እንየው ወይም፣ የተሻለ ዳኛ መድቡ ካስፈለገ በጽሑፍ በማመልክት ልጠይቅ አልኩ፡፡ ‹‹አይሆንም፤ ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ተሰብስቦ እስኪመደብ ጊዜ ያልፋል የሚል ምክር ቢጤ መጣ፡፡

ለደኅንነቴ ጥበቃ ለማግኘትም ሆነ ጉዳዩ በሦስት ዳኞች እንዲታይ ያደረግሁት ጥረት አልተሳካም፡፡ ረጅም ቀጠሮ እንድሰጥ ወይም የውሳኔውን ይዘት በተመለከተ ያየሁት ዳርዳርታ አላስደሰተኝም፡፡ በውሳኔው ይዘት ላይ ከተለያየ አቅጣጫ ተጽእኖ በርትቶ ስነበረና ወቅቱ የሰኔ መጀመሪያ 1997 በከተማው ውስጥ በነበረው የሰላም ሁኔታ የጻፍኩትን ውሳኔ ማንበብ የማያስችለኝ ቢሆንም የማላምንበትን ለመሥራት ደግሞ ህሊናዬ አልፈቀደልኝም፡፡

ስለዚህ ውሳኔውን ማንበቡን ተውኩትና መዝገቡ ሳይወሰን አደረ። ይመስለኛል፥ ዛቻዎችም እየጠነከሩ ስለነበር ያንን መዝገብ እኔ እንደምሰራው ተጠብቆ ነበር፡፡ በተራዬ እረፍት የምወጣበት ጊዜ ስለነበር ቀጥለው የገቡት ሌላኛው ዳኛ መዝገቡ ላይ ያመኑበትን ውሳኔ ሰጡ፡፡

በኋላ ጉዳት ከደረሰብኝ በኋላ እያጣራሁ ስሄድ እንደተረዳሁት ሌላኛው ዳኛ (በልምድ እንደሚበልጡኝ እየታወቀ) የሰሩትን ውሳኔ እኔ ጽፌ እንደሰጠኋቸው ተደርጎ የመንግሥት አካላት ለሚባሉት ሪፖርት ተደርጓል፡፡ የተባለው እኝህ ዳኛ የተባሉትን ውሳኔ አልሰሩም፤ ትዕዛዞቹንም አልሰጡም፤ ብርሃኑ ራሱ እየሰራ ፈርሙ ብሏቸዋል፤ ስምዎት ጋዜጣ ላይ ይወጣል ብሎ አሳመናቸው የሚል ነው፡፡ ይህን የፈጠራ ታሪክ ማን እና ለምን እንዳቀናበረው ባላውቅም፤ መዘዙ ግን ከባድ ነበር፡፡ ምንም ሆነ ምን ሌሎቹን መዝገቦች እኔ እንዳልሰራሁ ከተጣራና ከተረጋገጠ በኋላም፤ መጀመሪያውኑ ብርሃኑ ውሳኔውን በዚያ መልክ መወሰኑ ለሌሎች ዳኞች ድፍረት ሰጥቷል ወይም በሌላ መልኩ እንዳይወስኑ መንገድ ዘግቷል ወደሚል ውሃ የማይደፋ ትርክት ተቀየረ፡፡

እኚህኛው ዳኛ ደግሞ የነበረውን ሂደት ሁሉ ይስሙ አይስሙ አላውቅም፡፡ ሌሎቹ የሚጠብቁት እኔን ነው፤ ክትትሉም፣ ምኑም፣ ጫናውም እኔ ላይ ነው የነበረው፡፡ ሆኖም ዳኛው መሆን ያለበትን፣ ያመኑበትን፣ ሕግ ጠቅሰው እንደወሰኑ አስታውሳለሁ፡፡ በአጠቃላይ ውሳኔያቸው ምርጫ ቦርድ የሰራው ስህተት ነው የሚል ይዘት እንዳለው አስታውሳለሁ፡፡ ይመስለኛል ውሳኔያቸው ታትሟል፡፡ ከሳሽ የነበረው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የተሰኘው ፓርቲ ነው፡፡

ሌላው ትልቅና ችግር ያመጣብኝ ሆኖም ብዙም ትኩረት ሲስብ ያልሰማሁት ጉዳይ አለ፡፡ አንድ ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው (ብዙም አባላት የሉትም የሚባል) ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ‹‹የምርጫ ውጤቶች ይሰረዙልኝ›› የሚል ፋይል ከፈቶ ነበር፡፡ አንድ ዳኛ ክስ ሲቀርብለት በመጀመሪያ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን አለኝ ወይስ የለኝም የሚለውን፣ ጉዳዩ ያስከስሳል ወይስ አያስከስስም የሚለውን ያያል፡፡ በዚህ አግባብ መዝገቡን ስመረምርና ከከሳሹ እንደተረዳሁት የፓርቲው ተወዳዳሪዎች በተጠየቀው የምርጫው ቦታ አልተወዳደሩም፡፡ ካልተወዳደሩ ታዲያ ለምን ሊከስሱ እንደቻሉ ብጠይቅ ‹‹እርስዎ በሌላው ፋይል ላይ ሲቪክ ማህበራት ዓላማቸው ላይ ባይገለጽም ምርጫውን ይታዘቡ ብለው ስላሉና በፓርቲነቴ ምርጫን በተመለከት መክሰስ መብቴ ስለሆነ ነው›› የሚል ብቻ ነበር፡፡

ስለዚህ፣ አንደኛ ምርጫው ላይ አልተወዳደሩም፤ ሁለተኛ ነገር ደግሞ ምርጫ ቦርድ ጋር ሄደው አላመለከቱም፤ ወይም ሥነሥርዓቱን አልጨረሱም፡፡ ሦስተኛ ደግሞ ይሄንን በተመለከተ ደረስ የሚሉትን በደል በተመለከተ የቀረበ ማስረጃ ባለመቅረቡ የተሟላ ባለመሆኑ ፋይሉን ዘጋሁት፡፡

ከዚህ በኋላ ነገሮች እጅግ እየባሱና እየከፉ መጡ፡፡ (እኔን ወጥመድ ውስጥ ለመክተት ሙከራዎችንም አስተውያለሁ) በኋላ እንደሰማሁት ምርጫ ይሰረዝ ብለው ተቃዋሚ ፓርቲ ክስ የተመሰረተበት ታዋቂ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ያሸነፉበት መሆኑን በኋላ ተረድቻለሁ፡፡ የክሱ አላማ ምን እንደነበር መገመት ብችልም፤ በትክክል ግን አላውቅም፡፡ ይሄ ነገር በወቅቱ ብዙም ሲነገር ያልነበረ ነው፡፡

በግል ጥላቻ ይሁን በሌላ ባላውቅም አራት ኪሎ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አቅራቢያ በመኪና ከመገጨት በእግዜር ፈቃድ ተረፍኩ፡፡ ያኔ ከዳኝነት መልስ በእግሬ ነበር የምጓዘው፡፡ አስታውሳለሁ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ጋር ጥግ ጥግ ይዤ ስሄድ ልክ ከመንገድ የወጣ በማስመሰል ሊገጨኝ ሲል በአጋጣሚ መንገድ ስለቅ ነው የተረፍኩት እንጂ ወይ ሞት ወይ የአካል ጉዳት ይደርስብኝ ነበር፡፡

እንዲህ እንዲህ እያሉ መተንኮስ፣ ማሸማቀቅ፣ በግል ሰፈሬ ውስጥ የመንግሥት ወታደሮች ነን የሚሉ ሽጉጥ እስከ መምዘዝ ደረሱና ከፈለግን በማንኛውም ሰዓትና ጊዜ ልንገልህ እንችላለን አሉኝ፡፡ በኑሮዬ እና እንቅስቃሴዬ ሁሉ ደህንነት እንዳይሰማኝ፤ ጥርጣሬና ፍርሃት ውስጥ እንድወድቅ አበክረው ይሰሩ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሞራሌን ለመስበር ነው፡፡ የተለያዩ የማዋረድ ድርጊቶች ነበሩ፡፡ አባቱ ደርግ፣ ልጁ ቅንጅት እያሉ ተለጣፊ ስም መስጠት የተካኑበት ነበር፡፡

ይሄን ሁሉ ሪፖርት አድርጌያለሁ፤ ግን ሰሚ አላገኘሁም፡፡ በእርግጥ በእነርሱም አልፈርድም፤ ወቅቱ በጣም ከባድ ጊዜ ነው፤ በነርሱ ላይ ያለው ጫናም ትልቅ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ የሥራ ባልደረቦቼ ቸልተኝነት ከክፋት ብቻ እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡ በእኔ በአንድ ዳኛ ላይ እንዲህ ዓይነት ጫና አርፎ፣ በእነርሱ (በኃላፊዎቹ) ላይ ደግሞ ሊከብድ ይችላል በሚል ተረድቼ አልፌዋለሁ፡፡ እኔን ለመርዳት ቢሞክሩ በእነርሱ ላይ ሊመጣባቸው የሚችለውን መከራ እረዳለሁ፡፡ ስለዚህ ይሄን በመረዳቴ ብዙም አልተጫንኳቸውም፡፡

ከዚህ በኋላ በቀጥታ አስተዳደራዊ ጫና ከውስጥ ይመጣ ነበር፡፡ በዳኝነት ሥራዬ ላይ እኔን ወደ ማንሳፈፉ ሄዱ፡፡ ቦታዬ ላይ ሌላ ዳኛ ተመደበ፡፡ ሞራሌ እንዲነካ ምንም ሥራ እንዳልመደብ ተደረገ፤ ግን ደመወዝ ይከፍሉኛል፡፡

ዛቻ መጥቷል፣ ሪፖርት አደረግኩ፤ አስተዳደሮቹ ሊያዩልኝ አልቻልኩም፤ የማስፈራራት ድርጊቶች ተፈጽሞብኛል፡፡ ከዛ ብስጭት ውስጥ ገባሁ፡፡ በዛ ወቅት ደግሞ የድህረ ምረቃ የሕግ ትምህርት ክፍል ተመራቂ ተማሪ ነበርኩ፡፡ ግን የመመረቂያ ጽሑፌን ለመጨረስ ዳታ ብሰበስብም፣ ረቂቁን ብሰራም ግን መጨረስ አቃተኝ፤ መረጋጋት አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ አማካሪዬን ፕሮፌሰር ዘካሪያስ ቀንአ ይባላሉ፣ የገጠመኝን ሁኔታ ነገርኳቸውና መመረቂያ ወረቀቴን አራዘምኩት፤ (ፕሮፌሰር ዘካሪያስ በዛ መጥፎ ጊዜ ውስጥ የተረዱኝና የተተባበሩኝ ሰው በመሆናቸው ሳላመሰግናቸው ማለፍ አልችልም)፡፡

ከዛ ሰኔም በዚሁ አለፈ፤ ሐምሌም እንዲሁ መጣ- ሄደ፤ ክረምቱን በስቸጋሪ ሁኔታ አለፍኩ፡፡ በመስከረም መጨረሻ 1998 ዓ.ም ሥራ እንጀምር ነበር፡፡ ከፍርድ ቤትም አንድ ዳኛ ታሰሩ፡፡ የተገለጸው ምክንያት ሙሥና ፈጽመዋል ነው፡፡ ዳኛው በፍርድ ቤት 8 ዓመት ተቀጡ፡፡ ክሱ ተቀናብሮ ይሁን አይሁን አላውቅም፤ ነገር ግን ዳኛው ጎበዝና ትጉህ ዳኛ እንደነበሩ ግን አውቃለሁ፡፡

እኔን ደግሞ በመዋቅራዊ ሁኔታ ሲመቱኝ ወደ ጋምቤላ በተዘዋዋሪ ችሎት ሥራ ብለው መደቡኝ፡፡ ያኔ (98 መጀመሪያ ላይ) ሁኔታውን ሳጣራ ጋምቤላ ላይ ጸጥታው ጥሩ አይደለም ተባልኩ፡፡ ስለዚህ ወደዛ አልሄድም አልኩኝ፡፡ ምን እንደሚከተል አውቄ፤ ግን መጠንቀቅ ነበረብኝ፡፡ የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ለኔ በማሰብ ሂድ ብለው ለመኑኝ፡፡ ከፈለጉ ያባሩኝ፤ ከፈለጉም ይሰሩኝ እንጂ አልሄድም አልኳቸው፡፡ እያለ እያለ ጥቅምት ደረሰ፡፡ ጥቅምት ሃያ 1998 ዓ.ም አካባቢ አዲስ አበባ ዳግም አለመረጋጋት ተጀመረ፡፡ ስልክ ደውሎ አራት ኪሎ መጥተህ በመኪና ወደ ፍርድ ቤት እንውሰድህ ያለኝ ሰውም አለ፡፡ እንዴት ነው በእግሬ አራት ኪሎ ድረስ የምሄደው፤ ለሰፈሬ የሚቀርበኝ ካዛንቺስ ነው፤ አራት ኪሎ ያሉ ጓደኞቼ ጋር ደውዬ ሳጣራ እንደውም አራት ኪሎ ተኩስ ሁሉ አለ፤ ምን እየሆነ ነበር? እግዜር ይወቀው፡፡

ወደ ፍርድ ቤት ስልክ ደወልኩና ሰፈራችን ረብሻ ስላለ መምጣት አልችልም ብዬ ቀረሁ፡፡ 24 ሐሙስ ቀን ነው አስታውሳለሁ፡፡ በለሊት ሰፈር ውስጥ ሲፈልጉኝ ነበር፡፡ እንዴት ነው ይሄን ያጣራኸው ብትለኝ፣ ወደ ቤቴ ስገባ በዋናው መንገድ አልገባም፤ ባለጉዳይም ምንም ተከትሎ ስለሚያስቸግር ውስጥ ለውስጥ በመንደር ውስጥ ነው ወደ ቤት የምገባው፡፡ የራሴ መኖሪያ ቢኖረኝም ያኔ ለክፉም ለደጉ ቤተሰቦቼ ቤት ውስጥ ነበር የምኖረው፡፡ በመንደር ውስጥ ሁሉ እየገቡ ብርሃኑ የሚባል ዳኛ የት ነው ያለው እያሉ ከማለዳ ጀምሮ ሲያስሱኝ ነበር ያረፈዱት ለካ፡፡ ዳኛ ሲባል በተለምዶ ትልቅ ሰው ስለሚያስብ ነው መሰል አንድ ብርሃኑ የሚባሉ ሰው (አሁንም በህይወት ያሉ ይመስለኛል) ያሳዩዋቸዋል፤ እኔ እንዳልሆንኩ ሲያውቁ ተበሳጭተው ይሳደባሉ፡፡ በኋላ ለሥራ ጉዳይ የተፈለግኩ መስሏቸው አንድ ሰው ቤት ድረስ እየመሩ አመጧቸው፡፡

እነርሱ ሲመጡ ደግሞ እኔ የሰፈር ልብስ ነው የለበስኩት፤ ጅንስ ሱሪ አድርጌያለሁ፤ ከላይ ቲሸርት ነው ያደረግኩት፤ ወጣትነቴንም ፌቴ ይናገራል እኔ እሆናለው ብለው አላሰቡም፡፡ መጡ፤ በር አንኳኩ፤ ቀጥታ ወደ ቤት ገቡ፤ መሳሪያ የታጠቁ ናቸው፡፡ ስምንት ናቸው፡፡ ከዛም ዞሩና ወጡ፤ እኔን ይሆናል ብለው አልጠበቁኝም፡፡ በኋላ ትንሽ ወንድም አለኝ፤ እሱን ይሄ ልጅ የት ነው የሚሰራው አሉ፡፡ አይ ተማሪ ነው አልኳቸው፡፡ የትነው የሚማረው አሉ በቁጣ፡፡ የመሰለኝ የሆነ ሰው ፈልገው በማጣታቸው ሊደበድቡት እንደሆነ አሰብኩ፡፡ እኔ ደግሞ በወቅቱ ያወቁኝ ስለመሰለኝ የኔ ወንድም ነው ከቤትም ወጥቶ አያውቅም አልኳቸው፡፡ እውነትም ወንድሜ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት፤ ከቤት ትምህርት ቤት ነው እንጂ ሌላ ነገር ውስጥ አይሳተፍም፡፡

አንተ የት ነው የምትሰራው አሉኝ፤ ፍርድ ቤት፤ ማነው ስምህ፤ ብርሃኑ፤ ያኔ እየሮጡ መጥተው ይኸውና ተገኘ በሉት- በሉት ሲባባሉ የነበረ ጩኸታቸው አሁንም ጆሮዬ ላይ ያቃጭላል፡፡

 

img
ዳኛ ብርሃኑ ታዬ እንደሚተርኩት በምርጫ 1997 ወቅት በሰጡት ዳኝነት በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የደረሰባቸወው ድብደባ እስከዛሬም ጠባሳው አልሻረም። ታሪካቸውን የሚናገሩት ለወደፊቱ የዳኝነትነት ነጻነት እንዲረጋገጥ መታወቅ አለበት በሚል ነው።

እንግዲህ የመታነው በስህተት ነው እንዳይሉ ሰፈርተኛ ባለበት፣ አስሰው ቤቴ ገብተው ማንነቴን ጠይቀው ነው በደቦ ተሰባስበው የደበደቡኝ፡፡ ቢቸግረኝ ዶ/ር ብርሃኑን መስያቸው ይሆን ብዬ፤ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ነኝ ብዬ መታወቂያ ባወጣም ‹‹እናውቅሃለን የቅንጅት ዳኛ›› እያሉ እያፌዙ ተረባረቡብኝ፡፡ እኔ ብርሃኑ ነጋን (ፕሮፌሰር) በቴሌቭዥን ብቻ ነው የማውቃቸው፡፡ አግኝቻቸውም አላውቅ፡፡ ብርቱካን ሚደቅሳንም ዳኝነት ከለቀቀች ጀምሮ ተገናኝተን አናውቅም፡፡ የሁለቱን ስም እየጠቀሱ ገና ብዙ ምስጢር ታወጣለህ፣ ያለህን ግንኙነት ትዘረዝራለህ እያሉ ነው በዱላ በእርግጫ በቡጢ፣ በሰደፍ የሚደበድቡኝ፡፡

እየደበደቡኝም፣ ‹‹እነርሱ እንኳን አንተን ራሳቸውን አያድኑም- ታያታለህ›› እያሉ የመጡበትን ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡ በሌላ በኩል እኔን ሲያገኙ ታናሽ ወንድሜንም አልማሩትም፡፡ እርሱንም አብረው ነበር የሚደበድቡት፡፡ በወንድሜም አላቆሙም!

እናቴም ‹‹ኧረ! ልጆቼን›› ብላ ስትወጣ በጥይት ሊደፏት የመሳሪያውን መጠበቂያ ስቦ ከፍቶ ድግኖባት ነበር፡፡ እግዜር በጥበቡ አትርፏታል፡፡ እህቴም ሁሉ ተደብድባለች እስካሁን ጎኗን ያማታል፡፡ እነዚህ ሰዎች የፌዴራል ፖሊስ መለዮ የለበሱ ናቸው፡፡ አንድ መገናኛ የያዘ ነው የሚያዛቸው፤ እርሱ አማርኛም ይናገራል፡፡ ስድስቱ እኔን ሲደበድቡ፤ ሁለቱ ወደ ወንድሜ ሄደው ነበር፡፡

 

img
ዳኛ ብርሃኑ ታዬ፣ ያኔ የደረሰባቸው ጉዳት በእጃቸውም ላይ አስካሁን አለ።

ዱላው ሲበረታ ሮጠን ለማምለጥ በደመ ነፍስ ሞክረን ነበር፤ ግን መሳሪያ ሲደግኑ ምንም ማድረግ አልቻልንም ቆምን፡፡ የቻሉትን ያህል እየደበደቡ መጀመሪያ አንድ የሚሊተሪ ፒክ አፕ መኪና ላይ እየደበደቡን ጫኑን፡፡ ሌላም አንድ የፖሊስ ፒክ አፕ መኪና አለ፤ ከሰፈር ውስጥም የተወሰኑ ወጣት ወጣቱን ይዘዋል፡፡ ከጫኑን በኋላ ‹‹እነርሱን (እኔና ወንድሜን) ስድስት ኪሎ የሚሄደው ላይ ጫኗቸው አለ አለቅዬው፡፡ ስድስት ኪሎ ምን እንዳለ እኔ አላውቅም፡፡ ምናልባት አሉ ከሚባሉት ድብቅ እስር ቤት አንዱ ይሆናል፡፡

ከፖሊሱ ፒክ አፕ መኪና አውርደው ወደ ሚሊተሪ ፒክ አፕ መኪና ወረወሩን፡፡ ይሄ መኪና ደግሞ መትረየስ ተጠምዶበት፤ ወታደሩ ቃታው ላይ ጣቱን አስገብቷል፡፡ ቦታው በጣም ጠባብ በመሆኑ እግራቸው ሥር እንደበግ አስተኝተው እንደታረደ ዶሮ አናታችንን በከስክስ ጫማቸው ረግጠውናል፡፡ ጉዞ ወደ ስድስት ኪሎ ተጀመረ፡፡ ድርጊታቸው በሙሉ በአግባቡ የተዋቀረ ነው፡፡

በትክክለኛው ሁኔታ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛን እንኳን እንዲህ ልትደበድብ ይቅርና፣ ዳኛውን አንጓጠጥክ ተብለህ ሁሉ ነበር የምትታሰር፡፡ ሆኖም ያው ዲሞራላይዝ ማድረግ ነው የተፈለገው፤ እርሱንም በህዝብ ፊት በግላጭ አድርገውታል፡፡ በግምት አራት ኪሉ አደባባይ ጋር (መስቀለኛ መንገድ እንደሆነ ያስታውቃል) ለተወሰኑ ደቂቃዎች መኪናው ቆመ፡፡ ስንጓዝ ወዴት እንደሚወስዱን ለመረዳትና ለመለካት እሞክር ነበር፡፡ ቀጥታ ጉዞውንና መታጠፊያ ሥፍራዎችን ለመለየት ‹‹ሴንስ›› ለማድረግ እጥር ነበር፡፡ አደባባዩን ዞሮ ሲመለስ ሁሉ ይታወቀኛል፡፡ በቃ መንገድ ዝግ ስለሆነ ጥይት ቤት አቆዩአቸው ተባለ፡፡ ከዚያ ከፓርላማ ዞሮ ወደ አቧሬ መንገድ ጉዞ ቀጠለ፡፡ (በነገራችን ላይ ጥይት ቤት ማለት ከፓርላማው ወደ አቧሬ መንገድ ስትሄድ በስተቀኝ ያለው የወታደር ግቢ ነው) እዛ ወሰዱን፡፡

ጥይት ቤት እንደደረስን ከመኪና ሳንወርድ እንደገና ድብደባ ጀመሩ፡፡ እንግዲህ ፖሊሶቹ ለወታደሮቹ አስረክበውናል፡፡ እኛ ስድስት ኪሎ ነው የሚሄዱት ተብለን በወታደር ፒክ አፕ መኪና ላይ ነው የጫኑን፡፡ ከመኪና ስንወርድ ከሰፈርም የተያዙ ልጆችን እዛ አየኋቸው፡፡

እኔ በምያዝበት ጊዜ አንድ ጓደኛዬ ጋር በስልክ እያወራሁ ነበር፡፡ እና ከተያዝን በኋላ እህቴ እርሱ ጋር ደውላ እርሱ እና ሌሎች ደግሞ የሚያውቋቸው ሰዎች ጋር ደውለው ነው ሊያስፈቱን የቻሉት እንጂ ገና ብዙ አበሳችንን እናይ እንደነበር እየተዛተብን ነበር፡፡ ከመኪና በጎን በኩል ውረዱ አሉን፤ ሩቅ ነው፡፡ በስተጎን በኩል ልወርድ ስል ገፈተሩኝ፤ አንድ እግሬ ወደኋላ በመቅረቱ የግራ እግሬ በጎማውና በመኪናው አካል መካከል ገባ፡፡ አሸዋ፣ ጠጠር እና ኮረት ድንጋይ ላይ (ጥርጊያ መንገድ) በግራ ጎኔ ወደቅኩ፤ ያረፍኩበት ግራ እጄ እንደመላቀቅ ብሎ አልታዘዝ አለኝ፡፡ ሁለቱን ጣቶቼን በኋላ እስኪያሹልኝ ድረስ አልታዘዝ ብለውኝ ነበር፡፡ እንደገና በወደቅንበት ድብደባ ቀጠሉ፡፡

እየደበደቡን ሳለ ሌላ ልጆች ደግሞ ተይዘው መጡና እኛ ፋታ አገኘን፤ እነርሱን መደብደብ ጀመሩ፡፡ ሁኔታቸውን ላየ ባሳረፉት ዱላ ልክ የሚከፈላቸው ይመስል ነበር፡፡ በኋላም እኔን ለብቻ አደረጉኝ፡፡ ቢያንስ ብቻዬን ከሆነ የምሄደው በገባሁበት ጣጣ በራሴ እወጣዋለሁ፤ ታናሽ ወንድሜን ቢያንስ ከሌሎች እስረኞች ጋር ነው የሚወስዱት ምንም አይደለም በሚል ራሴን አረጋግቼ ቁጭ አልኩ፡፡

ከቆይታ በኋላ ላንድ ክሩዘር የሲቭል መኪና የያዙ ሰዎች እየተሯሯጡ መጡና ‹‹ብርሃኑ የሚባል ዳኛ እዚህ ታስሯል?›› ብለው ሲጠይቁ፡፡ ‹‹እረ በጭራሽ፤ እዚህ የለም›› ብለው ሊመልሷቸው ሲሉ ሰማሁ፡፡ እረ ብርሃኑ እኔ ነኝ፤ ብርሃኑ ነኝ እያልኩ ጮህኩ፡፡ ጮህኩ …

ሰዎቹ ድምጼን ሰምተው ወደ እኔ መጡ፡፡ መታወቂያዬን አሳየኋቸው፤ ጮሁ፤ ተቆጡ፡፡ ጓደኞቼ ይሄ ልጅ በምርጫ ጉዳይ ችሎት የታወቀ ነው፤ አውሮፓ ሕብረት የሚያውቀው ነው፤ የሆነ ነገር ሆነ ማለት የመንግሥት ሥም ይጠፋል ብለው እንዳሳመኗቸው እና የሚመለከታቸው ባለስልጣናት ልቀቁት የሚል ትእዛዝ እንደሰጡ ተረድቻለሁ፡፡ ውጣ ቢሉኝም ወንድሜን አይለቀቅም የሚሉ በመምጣታቸው፥ እሱ ካልወጣ አልሄድም በማለቴ እርሱም ወዲያው ተለቅቆ ቤት ድረስ ተሸኘን፡፡

የሆነው ሆኖ በጓደኞቼ ጥረት በዛው እለት ተፈታሁ፤ ግን ወጥቼ መተኛት እንኳ አልቻልኩም፡፡ በጀርባዬ መተኛት አልችልም፤ ጀርባዬ ተጎድቷል፡፡ በሆዴም መተኛት አልችልም፤ ሆዴ ነፍሯል፤ በጎኔ መተኛት አልችልም፤ ጎኔ ቆስሏል፡፡ ሰውነቴ በህመም፣ በድካምና በእንቅልፍ ዝሎ ግን መተኛት ያለመቻል ስቃይ፡፡

አንድ ሦስት ቀን ያህል ሥራም አልገባሁም፡፡ ቤት አረፍኩ፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚሰሩ ሐኪም ጓደኞች አሉኝ፤ በግሌ ተመረመርኩ፤ ታከምኩ፡፡

ፍርድ ቤት ውስጥ ሙያዊ አቅም የሚያንሳቸው፤ ችሎታ የሌላቸው፤ ሰዎች የብልግና ስደስብ፣ የማንነት ስድብ አእምሯዊና መንፈሳዊ ጥቃት ለመፈጸም ሞክረዋል፥ በጉዳቴም ተሳልቀዋል፡፡ ከዛም አልፈው‹‹ከፈለግን እኮ እንደፋኃለን›› ብለው ሽጉጥ ሲያሳይህ አእምሯዊ ጥቃት የፈጸሙም ነበሩ፡፡

ይህ ድርጊት የተፈጸመው (በህዝብ ፊት መንገድ ላይ መደብደቤ) ጥቃቱ ለእኔ ብቻ አይደለም፤ በፍትህ ሥርዓቱም ላይ ስለሆነ፣ ይጣራልኝ ብዬ ጠይቄ ነበር፡፡ ግን የፍርድ ቤቱ ምላሽ አጥጋቢ አልነበረም፡፡ ብዙ ሞራል የሚነኩ ነገሮች ነበሩ፡፡ ሆኖም፣ መጀመሪያ ራሴን አረጋጋሁ፤ ያለ ደመወዝ ለሦስት ወር ፈቃድ ወሰድኩ፡፡ ያለዛ ለእነርሱ መመቸት ነው፡፡ ሞራሌም ተነክቷል፤ ዳኛ ምንም አይነት ጥብቃ እንደሌለው ለሌላው በአሉታዊ መንገድ ማስተማርያ አድርገውኛል፡፡ ምን አምኜ ነው ሥሰራ የነበረው ያስብላል፡፡ አስተዳደሩ የማይጠብቅህ ከሆነ፣ መንግስት በክፉ አይኑ የሚያይህ ከሆነ፣ የመንግስት ኃይሎች አንተ ላይ እንዲህ ዓይነት ጥቃት የሚፈጽሙ ከሆነ፣ ይህ ሁሉ ሆኖብህም አንተ ምንም ማምጣት የማትችል ሰው (ዳኛ) ከሆንክ፤ ታዲያ ዳኝነት ምን ይፈይዳል!

እኔና ቤተሰቤ በፍርድ ሥርዓቱ ተጎጂ ነን፤ እንደ በቀል አድርገው ቤታችንን ነጥቀውናል፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን እኔ በዳኞቹ ብቻ አልፈርድም፡፡ እኛ (እኔም ባልደረቦቼም) ላይ የደረሰው ነገር የሚገልጸው አንድ ዳኛ ምንም ጥበቃ (ለደኅንነቱ/ቷ ዋስትና) እንደሌለው ነው፤ ስለዚህ በተቻለ መጠን የመንግሥት ጉዳይ ከሆነ ወስንለት እንጂ እንዳትወስንበት የሚል ያልተጻፈ መመሪያ ለህልውና ሲባል ገዢ ‹‹መርህ›› ቢመስል ሊደንቅ አይገባም፡፡ ይሄ በተግባር በዘዬ በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ ተዘርግቷል፡፡ የዳኞችን ሞራል (ስብእና) በመንካትና በማዋረድ ነው፡፡ ሁለተኛ የፓርቲ ንክኪ ያላቸውን በመሾም በፓርቲው የግንኙነት መስመር ለመቆጣጠር ተሞክሮ ሊሆን ይችላል፡፡

ይህ ለመንግሥት ተገዢ መሆንን ሊያመጣ ይችላል፤ ለመንግስት ተገዢ መሆን ማለት ደግሞ ለአስፈጻሚው አካል ተገዢ መሆን ማለት ነው፡፡ ይህ ሥልጣንን ለመቆጣጠርና ሚዛናዊ ለማድረግ የሚረዱት የሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና የሕግ አስፈጻሚ አካላት ድልድልና የእርስ በርስ ቁጥጥር ሚናን ያዛባል፡፡

ሥራህን ብቻ ስትሰራ የምታስቀይመው ይኖራል፥ ከዳኝነት ስትለቅ ውጪ ያለው አቀባበል ደስ የማይል ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዳኞቹ በዚህ የተነሳ ጫና ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ አንደኛ መንግስትን አትነካም፤ ሁለተኛ ለመንግስት ከሰራህ ማንም አይነካህም፤ ምናልባት ከፍርድ ቤት ተጣልተህ ብትወጣ እንኳ ውጭ ካለው ሰው ጋር ወዳጅ ታበጃለህ፤ ገንዘብ ታከማቻለህ፤ ስለዚህ ነገ ብባረር ልጆቼ ምን ይበላሉ? ስለዚህ ዳኛ ሆነህ ትንሽ ገንዘብ ሰብስብ የሚያስብል ሁኔታ የለምን? በተጨማሪም በደምሳሳው ስለዳኞች የሚነገረው በጎ ያልሆነ ነገር በኔ አስተያየት አብዛኛውን ቁጥር ይይዛሉ ለምላቸው ቅን ዳኞች የሚያስተላልፈው መልእክት ጥሩ አይደለም፡፡

በዚህ ላይ ከዳኝነት ሥራ ስትለቅ ለሁለት ዓመት ያህል ቀደም ሲል በሠሩበት ፍርድ ቤት በጥብቅና መስራት አይቻልም የሚል ሕግ አለ፡፡ ሕጉ በራሱ ክፋት የለውም፤ በዳኝነት ሥራ ላይ ሆነህ ከብዙ ዳኞች እና አስተዳዳሪዎች ጋር ባልደረባ ሆነህ ወዲያው ጠበቃ ሆነህ ሥራ ብትጀምር ፍትሕን ልታዛባ ትችላለህ፤ ፋይል አመቻችቶ ሊሄድ ይችላል ወዘተ ተብሎ ነው፡፡

ነገር ግን በሌላ በኩል፣ አብሮ መሰራት ያለበት ነገር አለ፡፡ እስቲ ቅን የሆኑትን ብዙዎቹን ዳኞች አስብ፤ ዛሬ ከሥራ ቢለቅ እስከ ሁለት ዓመት በሕግ ሙያው ጠበቃ ሆኖ ለመሥራት ያለውን ገደብ፡፡ ስለዚህ በሌሎች ፍርድ ቤቶች ሥራ ካላገኘ (በተለይ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበረና የሥራ ልምዱ አምስት ዓመት ካልሞላ) ያለው አማራጭ ምንድን ነው፤ ከጥብቅና ውጪ ሥራ ሊኖረው ይገባል፡፡

በእድሜው መሄድ ምክንያት ወይ በሌላ ምክንያት ራሱን አንድ ቦታ ካላበቃ ሥራ ባለማግኝት ቤተሰቡን ይዞ ይቸገራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ያለው አማራጭ ምንድን ነው ቀደም ብሎ ሙስና ውስጥ ይገባና ገንዘብ መሰብሰብ፤ አሊያም ትስስሮሽ (ኔት ዎርኪንግ) በመፍጠር ወዳልተገባ ተግባር ሊገፋው ይችላል፡፡እንደዚያም ሆኖ አሁንም ምርጥ ምርጥ ዳኞች አሉ፤ ከክፉ ይሰውራቸው እንጂ፡፡

አሊያም ከመንግሥት የዳኝነት ሹመቱ ላለመልቀቅ መንግስትን የሚያስደስት ነገሮችን እየሰራ፤ የተባለውን ሁሉ እየወሰንክ፣ ህሊናህ እየደማ በሹመትህ ትሰነብታለህ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ለዳኞች ክብር ስላልተሰጠ ነው፡፡ ጊዜ እየጠበቀ ዳኞችን የሚበቀል ሥርዓት ካለ እንዴት ነው ጥሩ ጥሩ ተተኪ ዳኞችን ሊያፈራ የሚችለው፡፡ ለምንድን ነው የፍትሕ ሥርዓቱ የወደቀው ብለህ ስትጠይቅ አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት ሀገሪቷ ለዳኞች የሰጠችው ክብር መውደቁ ነው፡፡ ዳኞች ጥበቃ የላቸውም፤ ዋስትና የላቸውም፤ በገቢም በኑሮም ተበድለህ ነው የምትኖረው፡፡ በእኛ ጊዜ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ሆኜ በእግሬ ነው የምሄደው፡፡ የባለጉዳዩን ቤት ተከራይቶ የሚኖር ዳኛ ገጥሞናል፡፡ እንግዲህ በዳኞች ላይ ያረፈውን ጫና አስበው፡፡ ከዚህ አልፎ ድብደባ፥ እንግልት፥ እስር ሲከተል፤ እንዴት ነጻና ገለልተኛ ዳኛ እንጠብቃለን?

እንደ ሀገር ዳኞች ላይ ያደረስነው በደል ነው የፍትሕ ሥርዓቱን የገደለው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ነው ሌላው የሚመጣው፡፡ እባካችሁ እናንተ የብዙኃን መገናኛ ባለሟሎች ዳኞችን በሙሉ አጥፊ በሚያስብል መልኩ ይልቀቁ የሚለው ነገር ፍትሓዊ እንዳልሆነ ብትገልጹ ደስ ይለኛል፡፡ አንደኛ ምን ያህሉ ዳኛ ነው ሌባ፣ ሙሰኛ፣ አድርባይ የሆነው፤ ለምንስ እንዲህ እንዲሆን እንደሆነ በማጥናት መፍትሄ መስጠት ነው ጠቃሚው፡፡ በሚዲያ እንደሰማሁት ለዳኝነት ክብር የማይመጥን ተግባር ያሳዩ፥ የሰብአዊመብትን የተጋፉ ዳኞች አሉ ቢባልም አጥፊውን ማረም እንጂ የዳኝነት ክብርና የተቋሙ ስም እንዳይዋረድ መጠንቀቅ ያሻል፡፡

በ1999 እኔ ከዳኝነት ስለቅ በአጠቃላይ ከፌደራል የመጀመሪያ ደረጃና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ከሥራ የለቀቁ ዳኞች ወደ ሠላሳ የሚጠጉ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ብቃት ያላቸው ጥሩ- ጥሩ ዳኞች ናቸው፤ ልምድ ያካበቱ ነበሩ፡፡ ይህ የለቀቁት ዳኞች ምናልባትም ፍርድ ቤቱ ካሉት ዳኞች አንድ አምስተኛው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ለፍትሕ ሥርዓቱ ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡

1999 ጥቅምት ወር ከፍርድ ቤት እንደለቀቅኩ በማስተማር ስራዬ ቀጠልኩ፤ ግን ቀጥሎ በዘዬ (ሲስተማቲክ) እኔን የማግለል ነገሮች ማየት ጀመርኩ፡፡ የምሄድበት ባለጉዳይም ሊሆን ይችላል፣ ተማሪህም ሊሆን ይችላል ድንገት ይቀየራል፤ ጥላቻ ያሳይሃል፤ ይርቅሃል፤ በመጀመሪያ ነገሩ አልገባኝም ነበር፤ ምን አድርጌ አስቀየምኳቸው እያልኩ ነበር የምሸማቀቀው፡፡ በኋላ ነው ‹‹ሲስተማቲክ›› የመንግሥት ኃይሎች ጥቃት ውስጥ መውደቄን ያወቅሁት፡፡

አንድ ቀን ሁለት የኔ ባለጉዳዮች በአንድ ላይ ሆነው ሻይ እየጠጡ አይተውኝ ይነጋገራሉ፤ አንደኛው የቅንጅት ደጋፊ የነበሩ ናቸው፤ ሌላኛው የገዢው ፓርቲ አካል ናቸው፡፡ እና እኔን ከርቀት ተመልክተው ያውልህ የእናንተ ዳኛ ይባባላሉ፡፡ የኢህአዴጉ ሰው ‹‹ቅንጅት›› ብሎ ፈርጆኛል፤ የቅንጅቱ ደጋፊ ‹‹ደንበኛ የወያኔ አገልጋይ›› አድርገው ቆጥረውኛል፡፡

በኋላ ጠርተውኝ ስናወራ ነው ከጀርባዬ የተሰራብኝ አሻጥር የገባኝ፡፡ ያኔ ነው ያ ‘የመንግሥት ደጋፊ’ የሆነው ሰው ፖለቲካውንም በቅጡ ስለሚያውቅ ‹‹ብርሃኑ ከባድ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለኸው፤ ከዚህ በኋላ ጠንቀቅ ማለት አለብህ፡፡ ሆን ተብሎ በአንተ ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር ከመጣ፤ ጥሩ ምልክት አይደለም፤ ከማህበረሰብ እየነጠሉህ ነው፤ ቀጥሎ በቀላሉ ነው የሚያጠቁህ›› አለኝ፡፡

በኋላ አስተውዬ መመልከት ስጀምር ዩኒቨርስቲ አካባቢም ይህን ሁኔታ ተረዳሁ፡፡ ዩኒቨርስቲ አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ መንግስትን አይወድም ስለሚባል የመንግሥት አካላት ነን የሚሉቱ እኔን በኢህአዴግ ሰውነት አስጠቁረውኛል፤ የደረሰብኝም የአደባባይ ጉዳት የሀሰት እንደሆነ ወሬ ነዝተዋል፡፡ ሆኖም፣ ጉዳት በደረሰብኝ ጊዜም ዩኒቨርስቲው ውስጥ 2ኛ ለማስተርስ ዲግሪ የመመረቂያ ጽሑፍ እያዘጋጀሁ ስለነበር ብዙዎች መጎዳቴን አይተዋል፤ አስተውለዋል፡፡ ለካ ድህረ ምረቃ የሕግ ትምህርቴን ስከታተል አብረውኝ እንደ ጓደኛ የነበሩ በሌላ ዲፓርትመንት ሲማሩ የነበሩ ሰዎች ይሄን ከጀርባዬ ሆነው እኔን መከታተልና ስሜን የማጠልሸት ስራ ይሰሩ ነበር፡፡ ሥሜን በሀሰት የሚያጠለሹትም ከዳኝነት በሥነምግባር ጉድለት እንደተባረርኩና በሆነ ጊዜ ልታሰር እንደምችል ያስወሩ ነበር፡፡ የመንግስት ደጋፊ ለሆኑ ደንበኞቼ ደግሞ ቀንደኛ የቅንጅት አባል እንደሆንኩ፤ ወደ ኋላም የግንቦት ሰባት አባል እንደሆንኩ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ ያስወሩና ማህበራዊ ደጀን እንዳይኖረኝ ይነጥሉኝ ነበር፡፡

አቶ መለስ ዜናዊን በተመለከተ

የምርጫ ውጤት ይታዘቡ አይታዙቡ የክስ መዝገብ ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንደሰጠሁና ጋዜጣ ላይ እንደወጣ፣ ከምርጫው ቀን (ከግንቦት ሰባት) በፊት ሃሙስ ዕለት የቀድሞ ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊ በቴሌቭዥን ቀርበው መግለጫ ይሰጣሉ፡፡ በመግለጫቸውም እግረመንገዳቸውን ስለምርጫ መታዘብ አስመልክተው ስም አይጥቀሱ እንጂ ስለ እኔ ነው ያወሩት ማለት ይቻላል፡፡ ‹‹የሃይማኖት ተቋማትን የምርጫ ታዛቢ እንዲሆኑ ስናደርግ፣ ለሃይማኖታቸው፣ ለፈጣሪያቸው ሲሉ ሃቁን ይናገራሉ ብለን ነው፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤት በማያገባው ገብቶ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን የሲቭክ ማህበራት እንዲታዘቡ ውሳኔ ሰጥቷል›› የሚል ይዘት ነበረው፤ አሁን የተናገሩትን ቃል በቃል ባላስታውሰውም፡፡

በማግስቱ ጠቅላይ ሚንስትሩ ያደረጉት ንግግር ላይ የፍርድ ቤቱን ክብር የሚነካ ንግግር ስላለው ‹‹የሀገሪቱ ጠ/ሚ የማያከብረውን ፍርድ ቤት፣ ማንም አያከብረውም›› በሚል በጉዳዩ ላይ ቀርበው ያስረዱ አሊያም ማስተባበያ መግለጫ ይስጡበት የሚል ትእዛዝ ለመስጠት አስቤ ጽፌ ነበር፡፡

ሆኖም፣ አጠቃላይ ነገሮችን ስመለከት ጥሩ ስላልነበሩ ተውኩት፡፡ የወጣ ትእዛዝ ሳይኖር እንዴት እንደሰሙ ባላውቅም፤ አቃቤ ሕግ በቅርቡ ደግሞ ዳኛ ሆነዋል ተብሏል ‹‹አንተ ማን ስለሆንክ ነው መለስን ቀርቦ ያስተባብል የምትለው!›› ብሎኛል- በንዴት ጦዘው፡፡ ይሄም ሰዎቹ ጥርሳቸውን እንዲነክሱብኝ ያደረገ ነው፡፡

ከ2001 ጅምሮ በግል ሕይወቴ የታዩ ለውጦችን ተከትሎ ትንሽ ነገሮች መስተካከል ጀመሩ፡፡ ምናልባት አደገ፣ ነፍስ አወቀ ብለውም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገሮች ላላ አሉልኝ፡፡ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ጫናው በእኔ ዙሪያ ባሉ ሰዎች ላይ በረታ፡፡ እኔን በተያዝኩ ጊዜ የረዱኝ፣ ያገዙኝ፣ ለማስፈታት የሞከሩ ሰዎች ሁሉ ሳይቀሩ ጫና ላይ ወደቁ፡፡ በዚህ በጣም ጭንቀት ውስጥ ወደቅኩ፡፡ በኔ ጦስ ችግር ውስጥ ወደቁ በሚል፡፡ በዚህ የተነሳ አላስፈላጊ ውጣ ውረዶችን ለማለፍ ተገደድኩ፡፡

በ2005 ጀምሮ በተለያየ ጫና ምክንያት ራሴን ከተለያዩ የሙያ ማኅበር፥ ማኅበራዊና የግል ጉዳዮች ለማግለል ተገደድኩ፡፡ ዝርዝሩ ይቆይ፡፡ ከዚህ በኋላ እኔ በጥብቅና ጉዳዮች እና ከምሠራባቸው ድርጅቶች ጋር በተያያዘ ችግሮች ይደርሱ ጅመር፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ወደ አለመያዝ አዘነበልኩ፡፡ በማውቃቸው ሰዎች በኩል ሳይቀር እኔን ጠልፎ ለመጣል የሚደረጉ ሙከራዎች መምጣት ጀመሩ፡፡ ስለዚህ ከዛ በኋላ ሰውን ማመን እየተውኩ መጣሁ፡፡ ቀስ እያልኩም ከነገሮች እየራቅኩ፤ ከጓደኞቼ ራሴን እያራቅሁ መጣሁ፡፡ ያለህበትን ሁኔታ ተረድተናል ሥራውን ተወው፤ አትስራልን! ካስፈለገ በየወሩ እንከፍልሃለን ብለው ቀናነት ያሳዩትን ግን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

ሁኔታውን አጤንኩና ሁለተኛ ማስተርሴን መማር ጀመርኩ፡፡ በዚህ ክፉ የጨለማ ቀናት ብጎዳም፣ በትምህርቴ እንድበረታ አድርጎኛል፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ጫና ውስጥ ብሆንም ሦስት ማስተርስና ሁለት ዲግሪ ይዣለሁ፡፡ ጫናውን ዝም ብዬ ተቀብዬው ቢሆን ኖሮ ይህን ጊዜ አእምሮዬ ተበላሽቶ ነበር፡፡ ከ2004 ጀምሮ የማታ መማር ጀመርኩ፡፡ ከዛ 2007 እና 2008 ሙሉ ቀን ተማርኩ፡፡ እንደገና ማታ ደግሞ ዲግሪ ተማርኩ፡፡ እየውልህ በእግዚአብሔር ጥበቃ በመማርና በራሴ ጭምር በመቀለድ ጫናዎችን አልፌያለሁ፡፡

በ2005 ሌላው የደረሰው ነገር፡ የአባቴን ቤት የመንግስት መሥሪያቤትን ሥም በመጠቀም እንዲለቅ ጠየቁ፡፡ በፍርድ ሥም አደረጉት፡፡ ይህ ድርጊት ብቻ አይደለም ህሊናን የሚያቆስሉ ነገሮች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ይመጣሉ፡፡ ጓደኛ በመምሰል፣ መንገድ ላይ የሚያውቅህ ሰው በመምሰል ‹‹ለኢህአዴግ ወግነህ ጋዜጣዊ መግለጫ ስጥና የቤተሰቦችህ ቤት እንዳይነጠቅ ማስደረግ እችላለሁ›› የሚል ሁሉ ተልኮ ይመጣል፡፡ እንግዲህ ዳኛ ሆኜ ባላውቅ ያን ያህል ውስጤን ባላመመኝ ነበር፡፡ ማስረጃ እያለው ነው አባቴ በመንግስት ሽፋን በጉልበተኞች ቤቱን የተነጠቅነው፡፡ (ዝርዝሩ ለጊዜው ይቆይ፡፡)

ከቤት አልወጣም ብለው ያንገራግራሉ ብለውም 2009 የካቲት እኔና አባቴን በግንቦት ሰባትነት፤ እናቴን ደግሞ በኦነግነት ለመክሰስ ምስክር ደልለው እንደነበር በኋላ መረጃ ደረሰን፡፡ ሽፋን የተደረገው መንግስት ቢሆንም፣ ቤቱን የነጠቁት ሲዝቱብንም የነበሩ ናቸው፤ ‹‹እኛ እዚህ ሀገር ላይ ደማችንን አፍስሰን፣ እናንተ ቀልዳችሁ አትኖሩም›› ይሉን የነበሩ ቡድኖች ናቸው፡፡

በጠቃላይ የማንም ፓርቲ አባል ስላለመሆኔ ቅንጅት የነበሩትም፥ ግንቦት ሰባትም ኢሀዴግም አሁን በነጻነት የሚነጋገሩበት ጊዜ በመሆኑ ማረጋገጥ አይከብድም፡፡ ውሳኔ የሰጠሁት፥ ያን ሁሉ ጫና የተጋፈጥኩት ለእውነት ስል እንጂ የትኛውንም ፓርቲ ለመጥቀም አልነበረም፡፡ ጉዳት ሲደርስብኝ በፖለቲካም ይሁን በግል ችግራቸው ምክንያት የተደሰቱና ሥራዬ ብለው የሐሰት ወሬ ያዛመቱብኝ አሉ፡፡ አንዳዶች ባለማወቅ ይህን ተከትለው ብዙ ነገር ብለውኛል፡፡ ለፍርድ ቤቱ ባያስቡ እንኳን ሰበዊነት ጎድሏቸው የሚሰጡት የ ‘በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት’ ትችት ሕመሙ ቀላል አልነበረም፡፡ አሁን ሁሉንም ትቼዋለሁ፥ ዋጋ የከፈልኩት ለእውነት ስል ነው፡፡ ከሌሎች ታሪኮች አንጻር እኔ ተነካሁ አልልም፥ እግዚአብሔር ተአምር በሚያስብል መልኩ አሳይቶ መልሶኛል፡፡ ነገር ግን ይህ የሆነብኝን ሁሉ ስናገረው ለእኔ ህመም ነው፤ ማስታወስም የማልፈልገው ሃቅ ነው፡፡ ይህን ታሪክ ያነበባችሁ ድጋሚ ባታነሱብኝ እመርጣለሁ፡፡ ድርጊቱ በሀገራችን እንዳይደገም፥ ፍርድ ቤቶች ሲሻሻሉ የዳኞች ደኅንነት ሊታሰብበትና የችግሩን ምንጭ ለማጤን በግብአትነት ይረዳ ዘንድ ብቻ ተናግሬዋለሁና!

አሁን በመጣው ለውጥ ነጻ ከወጡት ውስጥ ዋናው ነኝ ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሥራዬን እየሰራሁ ነው፤ የማስተማር ሥራዬንም ቀጥያለሁ፤ ወደ ቀድሞ የተረጋጋ ህይወቴ እየተመለስኩ ነው፡፡ ያለመሸማቀቅ በሙያዬ አገልግሎት እየሰጠሁ ነው፡፡ ተመስገን ነው፡፡

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.